#Fastmereja I የኦሮሞን ባህል፣ ቋንቋ፣ ወግ እና የቱሪስት መዳረሻዎችን በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚያስተዋውቁ ይዘት ፈጣሪዎችን (ኢንፍሉዌንሰሮችን) እውቅና ለመስጠትና ለማበረታታት ያለመ “የኦሮሞ ኢንፍሉዌንሰር አዋርድስ” የተሰኘ አዲስ የሽልማት መርሃ ግብር ይፋ ሆነ።
በጎዶ ኢቨንት ፕሮሞሽን እና በኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን ትብብር የተዘጋጀዉ ይህ መርሀ-ግብር ዋና ዓላማውም የኦሮሞ ሕዝብ ቁጥር ከፍተኛ ቢሆንም በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ያለው የዲጂታል ተደራሽነትና ተፅዕኖ አሁንም ከቁጥሩ ጋር የማይመጥን በመሆኑ ይዘት ፈጣሪዎች ጠንካራ የዲጂታል አሻራ እንዲያሳርፉ በማነቃቃት ይህንን ክፍተት መሙላት እንደሆነ አዘጋጆቹ ገልጸዋል።
በዚህ የመጀመሪያ ዙር የሽልማት መርሃ ግብር ላይ ከ200 በላይ የሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች የሚሳተፉ ሲሆን፣ ውድድሩ በቲክቶክ9፣ በፌስቡክ 3እና በዩቲዩብ 3 መድረኮች ላይ የተመሰረቱ 15 የተለያዩ የሽልማት ዘርፎችን ያካተተ ነው።
ከእነዚህም በተጨማሪ ሁሉንም ፕላትፎርሞች የሚያጠቃልል “የዓመቱ ምርጥ የኦሮሞ ኢንፍሉዌንሰር” እና የቱሪዝም መዳረሻዎችን የሚያስተዋውቁ ባለሙያዎች የሚሸለሙበት ልዩ የ”Best of Visit Oromia” ዘርፎች ተካተዋል። በውድድሩ በአንደኝነት ለሚያሸንፈው ተወዳዳሪ ታላቅ የመኪና ሽልማት የተዘጋጀ ሲሆን፣ ታዋቂ የሆኑ ሕፃናት የሚበረታቱበት የገንዘብና የቁስ ሽልማትም መመቻቸቱ ነዉ የተገለፀዉ።
የዕጩዎች ምርጫ የኦሮሞን ቋንቋ በንቃት መጠቀም፣ ባህልና አዎንታዊ ማኅበራዊ እሴቶችን ማስተዋወቅ እንዲሁም ለማኅበረሰቡ ዕድገት ገንቢ ተፅዕኖ መፍጠር በሚሉ ሦስት ዋና ዋና መስፈርቶች ላይ የተመሰረተ ነው።
የአሸናፊዎች አወሳሰን ሥርዓት 80 በመቶ በሕዝብ በቀጥታ ድምፅ የሚወሰን ሲሆን፣ ቀሪው 20 በመቶ ደግሞ ባህል፣ ታሪክና እሴት ሳይበረዝ በጥንቃቄ እንዲገመገም በታዋቂ ዳኞች የሚወሰን ተገልጿል።
ለአዋርዱ ከተለያዩ ዘርፎች የተመረጡት እጩዎች oiiaward.com ይፋዊ ድረ-ገጽ ላይ ቀርቧል።




