banner

ተደራሽ የቁጠባና ብድር ህብረት ስራ ማህበር የ9ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን አከበረ!

#Fastmereja:-ተደራሽ ማህበረሰብ አቀፍ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ኃላፊነቱ የተወሰነ የህብረት ሥራ ማህበር በአገር አቀፍ ደረጃ የቅርንጫፎቹን ቁጥር 33 በማድረስ እና ከ1.5 ቢሊዮን ብር በላይ አጠቃላይ ካፒታል በማፍራት የ9ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን በዛሬው ዕለት በድምቀት አክብሯል።

ማህበሩ በ4 ኪሎ የኢትዮጵያ ፖስታ ህንፃ ላይ በሚገኘው ዋና ቢሮው ባካሄደው የዚህ በዓል ስነ-ስርዓት ላይ የኢትዮጵያ ህብረት ሥራ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ጌትነት ታደሰ፣ ምክትል ኮሚሽነር አቶ አብዲ ሙመድ፣ የተቋሙ የሥራ አመራር ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ አልማዝ ኦልጅራ ጨምሮ የክልልና የከተማ አስተዳደር የሥራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የተደራሽ የቁጠባና ብድር ኃላፊነቱ የተወሰነ የህብረት ስራ ማህበር መስራችና ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አለማየሁ ታመነ እንደገለፁት ማህበሩ በሐምሌ ወር 2009 ዓ.ም በ24 መስራች አባላት እና በ24 ሺህ ብር መነሻ ካፒታል በአዲስ አበባ አራዳ ክፍለ ከተማ እንደተመሰረተ ያስታወሰው የተቋሙ መግለጫ፤ ባለፉት ስድስት ዓመታት ባደረገው ስትራቴጂካዊ የሪፎርም ንቅናቄ አሁን ላይ የአባላቱን ቁጥር ከ27 ሺህ 900 በላይ ማድረስ መቻሉን ይፋ አድርጓል።

ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ ለተከታታይ ሦስት ዓመታት በቤተሰብ ደረጃ ተወስኖ የነበረው ተደራሽ፣ ከመስከረም 2013 ዓ.ም ጀምሮ ባደረገው አዲስ የአሠራር ለውጥ በአገር አቀፍ ደረጃ ፈጣን ዕድገት ማስመዝገብ መቻሉ ተመላክቷል።

ተቋሙ እስካሁን ከ2,500 በላይ አባላትን የብድር ተጠቃሚ ያደረገ ሲሆን፤ 443 አባላትን የቤት ባለቤት፣ 452 አባላትን ደግሞ የሥራና የቤት መኪና እንዲሁም የባጃጅ ባለቤት ማድረግ ያስቻለ ሲሆን ተቋሙ በአጠቃላይ ከ13 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቀጥተኛና ቀጥተኛ ያልሆነ የሥራ ዕድል መፍጠሩም ተገልጧል።

የማህበሩን የቀጣይ አቅጣጫ በተመለከተ በተሰጠው ማብራሪያ፣ ተቋሙ በቀጣይ 17 አዳዲስ ቅርንጫፎችን በመክፈት አጠቃላይ የቅርንጫፎቹን ቁጥር 50 ለማድረስ ማቀዱን ገልጿል።

የዲጂታል ኮር ባንኪንግ ሥርዓቱን ይበልጥ በማጠናከር የአገሪቱን ማዕከላዊ የፋይናንስ ክምችት ለማሳደግ የድርሻውን እንደሚወጣ የጠቀሰው ማህበሩ፣ እ.ኤ.አ በ2029 ከአፍሪካ ምርጥ 10 የቁጠባና ብድር ተቋማት ተርታ ለመሰለፍ ትልቅ ራዕይ ሰንቆ እየሰራ እንደሚገኝ አስታውቋል።





Leave a Comment