banner

በጋሞ ብሔረሰብ የሙሽሮች ቁንጅና እና የትዳር ጥራት የሚመዘንበት “ሶፌ” ባህላዊ ክዋኔ ተከናወነ

​#FastMereja I በጋሞ ብሔረሰብ ዘንድ ያገቡ ሙሽሮች በህብረተሰቡ ዘንድ ይፋዊ ዕውቅና አግኝተው ወደ ማህበራዊ ህይወት የሚቀላቀሉበት እና የትዳር አያያዝ ጥራት የሚመዘንበት ባህላዊ የቁንጅና እና የእውቅና ስነ-ስርዓት (ሶፌ) ተከናውኗል። ይህ ባህላዊ ክዋኔ አዲስ ተጋቢዎች ከጋብቻ በኋላ ከ1 እስከ 4 ወራት በቤት ውስጥ ገንፎ፣ ቅንጬ፣ ጩኮ፣ ቡላ እና በማር የታሸ ቆሎ የመሰሉ ሰውነት ገንቢ ምግቦችን እየተመገቡ በጥንቃቄ ከተንከባከቧቸው በኋላ የሚፈጸም የማጠቃለያ ስነ-ስርዓት ነው።

​በዕለቱ ሙሽሮች በወዳጅ ዘመዶቻቸው ታጅበው፣ ጸጉራቸውን በቅቤ (ፑንጽሮ) አበጥረው፣ በከበረ ጨሌ፣ በጋሞ ባህላዊ የጥበብ ቀሚስ እና በሱፋሌ (ካባ) አጊጠው ወደ ገበያ በመውጣት ስርዓቱን ይፈጽማሉ። በስነ-ስርዓቱ መሰረት ሴት ሙሽሮች ገበያውን አራት ጊዜ፣ ወንድ ሙሽሮች ደግሞ ሶስት ጊዜ ከዞሩ በኋላ የተዘጋጀውን ጠላ በመጋበዝ የህዝቡን ምርቃት ይቀበላሉ። ህብረተሰቡ በእግረ መንገዱ የሙሽራዋን አቀራረብና ውበት በማየት የባሏንና የቤተሰቦቿን የእንክብካቤ ደረጃ በመገምገም ዕውቅና የሚሰጥ ሲሆን፣ ስነ-ስርዓቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ሙሽራዋ ሙሉ በሙሉ የማህበረሰቡ ንቁ ተሳታፊ በመሆን ወደ አዲስ የህይወት ምዕራፍ ትሸጋገራለች።

Leave a Comment