#FastMereja I በአዲስ አበባ ከተማ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ አያት አፓርትመንት አካባቢ ለምታኖረው ቤተሰቧ “ታግቻለሁ” በማለት ከቀድሞ ፍቅረኛዋ ጋር በመሆን 850 ሺህ ብር የካሳ ክፍያ የጠየቀችው ራሄል መለሰ የተባለች ግለሰብ በባህር ዳር ከተማ በሚገኝ ሆቴል ውስጥ ከነአባሪዋ በቁጥጥር ስር መዋሏን የአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አስታወቀ።
ግለሰቧ ሀምሌ 25 ቀን 2018 ዓ.ም ከቀኑ 4፡00 ሰዓት ላይ ከቤት ከወጣች በኋላ ባለመመለሷ ቤተሰቦቿ ለአካባቢው ፖሊስ አቤቱታ አቅርበው ነበር። ፖሊስ ፍለጋ ላይ በነበረበት ወቅት ለአባቷ ስልክ በመደወል ልጃቸው እንደታገተችና የተጠየቀውን 850 ሺህ ብር ካልላኩ በህይወት እንደማያገኟት ማስፈራሪያ ደርሷቸዋል።
የፖሊስ የክትትልና ኦፕሬሽን ቡድን ባደረገው ከፍተኛ ጥረት ተጠርጣሪዋ የታገተች አስመስላ ከቀድሞ ፍቅረኛዋ ሰለሞን ቁምላቸው ጋር በባህር ዳር ከተማ ስማዳ በሚባል አካባቢ ሆቴል ተሸሽገው እንደነበር ደርሶባቸዋል። ተጠርጣሪዎቹ ከሀገር ለመውጣት ገንዘብ ስላስፈለጋቸው ይህን ድርጊት ማቀዳቸውን በምርመራ አምነዋል። የአዲስ አበባ ፖሊስ በሁለቱም ላይ ተጨማሪ ምርመራ እያካሄደ ሲሆን፣ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ሲሉ በመሰል የሀሰት እገታ ወንጀል ውስጥ የሚሳተፉ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስቧል።
