banner

የዲያስፖራ ወጣቶችን ከሀገራቸው ጋር የሚያስተሳስር የውበትና ባህል ውድድር ይፋ ሆነ!

#Fastmereja:-የዲያስፖራ አባላትና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ከሀገራቸው፣ ከባህላቸውና ከህዝባቸው ጋር ያላቸውን ዘላቂ ቁርኝትና ትስስር ለማጠናከር የሚያስችል «ሚስ ጄኔሲስ ኢትዮጵያ» (Miss Genesis Ethiopia) የተሰኘ የውበት፣ የእውቀትና የባህል ውድድር ፕሮግራም መዘጋጀቱ በዛሬዉ እለት በተሰጠ መግለጫ ተገልጿል።

ፕሮግራሙን አስመልክቶ ጄኔሲስ ኢንተርናሽናል ኦርጋናይዜሽን ከኢፌዴሪ ዲያስፖራ አገልግሎት ጋር የመግባቢያ ስምምነት የተፈራረሙ ሲሆን የዲያስፖራ ልጆች ከሀገራቸው ጋር ጥብቅ ቁርኝት እንዲፈጥሩ ማለም ውድድሩ ከተቀረጸባቸው ዋና ዋና ምክንያቶች መካከል አንዱ መሆኑ ተገልጿል።

«ሚስ ጄኔሲስ ኢትዮጵያ» ከውጫዊ ውበት ባሻገር የእውቀት፣ የባህል ግንዛቤ፣ የመሪነት ብቃት፣ የፋሽን እውቀት፣ የብራንዲንግ ችሎታ እና ሀገሪቱን በዓለም አቀፍ መድረክ የመወከል ብቃትን እንደ መመዘኛ መስፈርት ያካተተ መሆኑ ተገልጿል።

ውድድሩን በከፍተኛ የፕሮዳክሽን ስታንዳርድ አዘጋጅቶ በየሳምንቱ በስድስት ክፍሎች ለማስተላለፍም ከኢቢኤስ ቴሌቪዥን (EBS TV) ጋር የትብብር ስምምነት ተፈራርሟል።

በውድድሩ ሂደት ከተመዘገቡት መካከል 50 ተወዳዳሪዎች በመጀመሪያው ማጣሪያ የሚያልፉ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ 20 መሪ ተወዳዳሪዎች በቴሌቪዥን በሚተላለፉት ስድስት ክፍሎች ይሳተፋሉ። የውድድሩ አሸናፊ በሰባተኛው ሳምንት በሚካሄደው ታላቅ የማጠቃለያ ሥነ-ሥርዓት ይፋ እንደምትሆን ታውቋል።

በመግለጫዉ ላይ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ክቡር አምባሳደር ፍፁም አረጋ እንደገለፁት፣ የወጣቶችን በራስ መተማመን የሚያሳድጉና ከሀገራቸው ጋር ጥብቅ ቁርኝት የሚፈጥሩ መሰል አላማ ያላቸውን ድርጅቶች በመደገፍ አብሮ የመስራት ዝግጁነታቸውን አረጋግጠዋል።

የውድድሩ ዝግጅት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ በቱሪዝም ሚኒስቴር፣ በአዲስ አበባ ቱሪዝም ኮሚሽን እና በኢቢኤስ ቴሌቪዥን በጥምረት የሚዘጋጅ ሲሆን፣ ተቋማቱ ዝግጅቱ የሀገሪቱን ገጽታ ለመገንባትና የቱሪዝም አቅምን ለአለም ለማስተዋወቅ ከፍተኛ ድርሻ ስላለው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

በተጨማሪም ወደፊት የሌሎች ሀገራት ተወዳዳሪዎችን በመጋበዝ ውድድሩን «ሚስ ጄኔሲስ ኢንተርናሽናል» በሚል ደረጃ ዓለም አቀፋዊ ለማድረግ መታቀዱ ተገልጿል።





Leave a Comment