#FastMereja I የአሜሪካው የትራምፕ አስተዳደር በኤርትራ የመከላከያ ሰራዊት እና በሀገሪቱ ሌሎች ተቋማት ላይ ተጥሎ የነበረውን የኢኮኖሚ ማዕቀብ ማንሳቱን የአሜሪካ Department of the Treasury ይፋ ባደረገው መግለጫ አስታውቋል።
ይህ የዋሺንግተን ውሳኔ የመጣው አሜሪካ ስትራቴጂካዊ በሆነው የቀይ ባህር ቀጠና ላይ ትኩረቷን ዳግም ባጠናከረችበት ወቅት ነው። የኤርትራ የባህር ዳርቻ ከሳውዲ አረቢያ ተቃራኒ የሚገኝ በመሆኑና በአካባቢው ያለው የወደብና የንግድ መስመር ውጥረት በመጨመሩ፣ የአሜሪካ መንግስት ከኤርትራ ጋር ያለውን ግንኙነት እንደገና ለመቃኘት መወሰኑ ተገልጻል።
እንደ ቲአርቲ አፍሪካ ዘገባ፤ የቀድሞው የጆ ባይደን አስተዳደር በፈረንጀቹ 2021 በኤርትራ የመከላከያ ሰራዊት፣ በገዢው ፓርቲ እንዲሁም በተወሰኑ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት እና የንግድ ተቋማት ላይ ማዕቀብ ጥሎ ነበር። በወቅቱ ማዕቀቡ የተጣለው የኤርትራ ሰራዊት በትግራይ ክልል በነበረው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ውስጥ በነበረው ተሳታፊነት ምክንያት እንደነበር ይታወሳል።
አሁን የተነሳው ማዕቀብ የመከላከያ ሰራዊቱን፣ የመንግስት የንግድ ድርጅት የሆነውን እና የፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ የኢኮኖሚ አማካሪ የሆኑትን አቶ ሀጎስ ገብረህይወትን ጨምሮ ሌሎች አካላትን ያካተተ እንደሆነ ተጠቅሷል። የኤርትራ የማህበራዊ ኮሙኒኬሽን ሚኒስትር አቶ የማነ ገብረመስቀል አሜሪካ የጣለችውን ማዕቀብ ማንሳቷን ሀገራቸው በጥሩ ሁኔታ እንደምትቀበለውና ውሳኔውን እንደሚያደንቁት ገልጸዋል።
