#FastMereja I በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ጥቂት የማይባሉ ዓለም አቀፍ እና የግል ትምህርት ቤቶች ለ2026/27 የትምህርት ዘመን የሚያስከፍሉትን ከፍተኛ ዓመታዊ የትምህርት እና የምዝገባ ክፍያ ይፋ አድርገዋል። ከእነዚህም መካከል ኢንተርናሽናል ኮሙዩኒቲ ስኩል (ICS Addis)፣ የጀርመን ኤምባሲ ትምህርት ቤት እና ሊሴ ገብረ ማርያም ግንባር ቀደም ተጠቀሾች ናቸው።
በአውሮፓውያኑ 1964 የተመሠረተው ኢንተርናሽናል ኮሙዩኒቲ ስኩል (ICS Addis) ለቀጣዩ የትምህርት ዘመን ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት፣ የክፍያ መጠኑ እንደ ተማሪዎቹ የክፍል ደረጃ የሚለያይና በዶላር የሚሰላ ነው። በዚህም መሠረት ከ3 እስከ 4 ዓመት ላሉ ሕፃናት ዓመታዊ ክፍያው 19 ሺህ 495 ዶላር (ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ) ሲሆን፣ ለ11ኛ እና 12ኛ ክፍል ተማሪዎች ደግሞ እስከ 37 ሺህ 215 ዶላር (ወደ 5.98 ሚሊዮን ብር ገደማ) ይደርሳል። በተጨማሪም ትምህርት ቤቱ ለአዳዲስ ተማሪዎች የምዝገባ እና የትምህርት ቤት ማሻሻያ ተጨማሪ ክፍያዎችን ያስከፍላል።
በሌላ በኩል የጀርመን ኤምባሲ ትምህርት ቤት በድረ-ገጹ ባወጣው መረጃ፣ ክፍያው በየተቋማቱ በሚሸፈንላቸው እና በራሳቸው በሚከፍሉ ወላጆች መካከል ልዩነት እንዳለው አመልክቷል። ወላጆቻቸው በሚሠሩባቸው ተቋማት ክፍያቸው የሚሸፈንላቸው የ11ኛ እና 12ኛ ክፍል ተማሪዎች በዓመት 20 ሺህ 803 ዩሮ (ከ3.8 ሚሊዮን ብር በላይ) የሚከፍሉ ሲሆን፣ በራሳቸው ለሚያስተምሩ ደግሞ 8 ሺህ 808 ዩሮ (1.6 ሚሊዮን ብር ገደማ) ተተምኗል። በተመሳሳይ መልኩ ከ1948 ዓ.ም ጀምሮ አገልግሎት የሚሰጠው ሊሴ ገብረ ማርያም ትምህርት ቤት እንደ ተማሪዎቹ ዜግነት ልዩነት ያደረገ ሲሆን፣ ለሁለተኛ ደረጃ የውጭ ዜጎች እስከ 9,550 ዩሮ (ከ1.7 ሚሊዮን ብር በላይ)፣ ለኢትዮጵያውያን ደግሞ በዓመት 420 ሺህ ብር ክፍያ ወስኗል።
የአዲስ አበባ የግል ትምህርት ቤቶች አሠሪዎች ማኅበር ሥራ አስኪያጅ አቶ አጽብሃ አብርሃ ለጉዳዩ በሰጡት አስተያየት፣ የትምህርት ተቋማት የሚያስከፍሉት ከፍተኛ ክፍያ የመምህራን ደመወዝ፣ የአስተዳደር ወጪዎች እና የትምህርት ግብዓቶችን ለማሟላት ከሚወጣው ከፍተኛ ወጪ ጋር የተያያዘ መሆኑን ገልጸዋል። በከተማዋ ከ1,500 በላይ የግል ትምህርት ቤቶች እንደሚገኙ የጠቆሙት ሥራ አስኪያጁ፣ የተቋማቱ ባለቤት መሆን ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ መሆኑን አስረድተዋል።
ምንጭ፦ ቢቢሲ አማርኛ
