banner

አቢሲንያ ግሩፕ ኦፍ ኢንዱስትሪ ያስገነባውን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት አስረከበ

#FastMereja I ​አቢሲንያ ግሩፕ ኦፍ ኢንዱስትሪ በድርጅቱ የቀድሞ ቼርማን አቶ ማሄንድራባይ ፓቴል መታሰቢያነት በቢሾፍቱ ከተማ ያስገነባውን “ኤጂአይ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት” አስመርቆ ለአካባቢው ማህበረሰብ አስረከበ። የትምህርት ቤቱን ግንባታ እና የመማሪያ ቁሳቁሶችን ሙሉ በሙሉ አሟልቶ ለማስረከብ ከ106 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉን የድርጅቱ አድሚኒስትሬቲቭ ማናጀር አቶ ሄኖክ ደምስ እና የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጃቲን ፓቴል ገልጸዋል።

​እንደ ድርጅቱ አመራሮች ገለጻ፤ ትምህርት ቤቱ ሙሉ በሙሉ የተሟሉ እና ዘመናዊ ቁሳቁሶች ያሏቸው 8 ክፍሎች ያሉት ሲሆን፣ በአንድ ጊዜ እስከ 380 ተማሪዎችን የማስተናገድ አቅም አለው። በተጨማሪም ድርጅቱ ለተማሪዎቹ ለአንድ ዓመት ሙሉ ነፃ የምግብ አገልግሎት፣ የጽዳት እና የጥበቃ አገልግሎቶችን ሙሉ በሙሉ እንደሚሸፍን የተገለጸ ሲሆን፣ ተማሪዎችም ያለ ምንም ክፍያ በነፃ የሚማሩበት የመንግስት ትምህርት ቤት ሆኖ የሚያገለግል ይሆናል።

​አቢሲንያ ግሩፕ ኦፍ ኢንዱስትሪስ ድርጅቱ በሚገኝበት ቢሾፍቱ ከተማ ለሚኖሩ ማህበረሰቦች እና ለሰራተኞቹ ቤተሰቦች ጥራት ያለው የትምህርት እድል ለመፍጠር በማሰብ ይህንን ፕሮጀክት እውን ማድረጉን ጠቅሶ፣ ከዚህ ቀደምም በአካባቢው የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት እና የተለያዩ የማህበራዊ ድጋፍ ስራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን ገልጿል። በተጨማሪም በከተማዋ በሚገኙት የማምረቻ ፋብሪካዎቹ አማካኝነት ለሺዎች የሚቆጠሩ የአካባቢው ነዋሪዎች የሥራ ዕድል መፍጠሩን አብራርቷል።

ዝግጅቱን ያስተባበረው ኤልቬዜት ኢንተርናሽናል ኢቨንትስ ሲሆን ​በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የትምህርት ባለሥልጣናት፣ የሃይማኖትና የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም የአካባቢው ነዋሪዎች የተገኙ ሲሆን፤ የድርጅቱ አመራሮች ለኢትዮጵያ መንግሥትና ለቢሾፍቱ ህዝብ ላደረጉት ቀጣይነት ያለው ትብብር ምስጋና አቅርበዋል። አቢሲኒያ ግሩፕ በኢትዮጵያ፣ ኬንያና ኡጋንዳ የሚንቀሳቀስ ምስራቅ አፍሪካዊ ኩባንያ እንደመሆኑ መጠን፣ የማህበራዊ ኃላፊነቱን በመወጣት በሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገት ላይ አወንታዊ አስተዋጽኦ ማድረጉን እንደሚቀጥል አስታውቋል።





Leave a Comment