#Fastmereja:- በየቀኑ የምግብ ገበታችን ላይ የሚቀርበውና ለጤና እጅግ አስፈለጊ እንደሆነ የሚነገርለት ወተት፣ በሂደቱ ውስጥ ተገቢው ጥንቃቄ ካልተደረገበት ለከባድ ህመም የሚያጋልጥ የምግብ አይነት እንደሆነ ተገለፀ።
ብዙዎቻችን ወተትን የምንመለከተው እንደ ንጹህና አልሚ ምግብ ቢሆንም፣ ከእርሻ እስከ ተጠቃሚው ጭልፋ በሚደርስበት ረጅም መንገድ ውስጥ ግን ከፍተኛ የጥራትና ደህንነት ጥንቃቄ ይፈልጋል።
የኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን (EFDA) ባወጣው መረጃ መሰረት፣ በወተት እሴት ሰንሰለት (Value Chain) ውስጥ በሚፈጠር ማንኛውም መዘናጋት ምክንያት አደገኛ ባክቴሪያዎችና ጎጂ ህዋሳት በምርቱ ላይ ሊራቡ እንደሚችሉ አስታዉቋል።
የወተት ደህንነት እንዳይበላሽ እነዚህ የፍተሻ መንገዶች (Checkpoints) ወሳኝ ድርሻ አላቸው፦
1.የከብቶች መኖና ንፅህና ፦ጤናማና ደህንነቱ የተጠበቀ ወተት የሚገኘው በቅድሚያ ከጤናማ ላሞች ሲሆን አርሶ አደሮችና አርቢዎች ለላሞች የሚሰጡት መኖ ከሻጋታ፣ ከመርዛማ ኬሚካሎችና ከባክቴሪያ ነፃ መሆኑን ማረጋገጥ አለባቸው። በተጨማሪም የላሞች መጠለያ ንፅህና እና የእስትንፋስና የአካል ጤንነት መደበኛ ክትትል ሊደረግበት ይገባል።
2.ደህንነቱ የተጠበቀ ማጓጓዝ :-ወተት ከታለበ በኋላ በፍጥነት ወደ ማቀነባበሪያ ወይም ወደ ገበያ በሚጓጓዝበት ወቅት ጥራቱን እንዳያጣ የሙቀት መጠኑ ተጠብቆ በቅዝቃዜ ማጓጓዝ (Cold Chain) ወሳኝ ሲሆን ወተቱ የሚጓጓዝበት ዕቃ (Tanker) ደረጃውን የጠበቀ፣ ከዝገትና ከቆሻሻ ነፃ በሆነ ንፁህ የብረት መያዣ መሆን አለበት።
3.የማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች ቁጥጥር:- በማቀነባበሪያ ማዕከላት ውስጥ በሚደረጉ ሂደቶች ወተቱን ከጎጂ ባክቴሪያዎችና ተህዋሲያን ነፃ ለማድረግ የፓስቸራይዜሽን እና የማከም ስራዎች በከፍተኛ ጥንቃቄ መጠናቀቅ አለባቸው። ባለሙያዎችም በሂደቱ ወቅት አስፈላጊውን የንፅህና መጠበቂያ አልባሳትና መሳሪያዎች በመጠቀም ጥራቱን ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል።
4.የአከፋፋዮችና የችርቻሮ ነጋዴዎች ኃላፊነት :-ወተት፣ አይብ፣ እርጎና ሌሎች የወተት ተዋጽኦዎችን ለህብረተሰቡ የሚያቀርቡ አከፋፋዮችና የሱቅ ነጋዴዎች ምርቶቹን ከመሸጣቸዉ በፊት የማቀዝቀዣ ፍሪጅ ውስጥ ማስቀመጥ አለባቸው። የወተቱን የመጠቀሚያ ጊዜ (Expiry Date) ማረጋገጥና ምርቱ ለፀሐይ ብርሃን ወይም ለከፍተኛ ሙቀት እንዳይጋለጥ ማድረግ የነጋዴዎች ግዴታ ነው።
5. የመጨረሻው የደህንነት መስመር የደንበኞች አጠቃቀም ሲሆን ህብረተሰቡ ያልተቀነባበረ ወተት ሲገዛ ከመጠቀሙ በፊት በደንብ ማፍላት፣ በንፁህ እቃ ውስጥ አሽጎ ፍሪጅ ውስጥ ማስቀመጥ እና ንፅህናቸውን የጠበቁ ምርቶችን ብቻ መግዛት እንዳለበት ተመላክቷል።
የምግብ ደህንነትን ማረጋገጥ የአንድ አካል ሀላፊነት ብቻ ሳይሆን የአምራቾች፣ የአጓጓዦች፣ የነጋዴዎችና የተጠቃሚው ህብረተሰብ የጋራ ኃላፊነት ሲሆን እያንዳንዱ አካል በየደረጃው የሚጠበቅበትን ጥንቃቄ በማድረግ የራሱንና የቤተሰቡን ጤና እንዲጠብቅ ጥሪ ቀርቧል።
በማንኛውም ሁኔታ ጥራትና ደህነነቱ ያልተረጋገጠ ወተት ካጋጠመዎት ወደ 8482 በነፃ በመደወል ጥቆማ ይስጡ









