banner

ኢትዮጵያ የ2027ቱን የአፍሪካ የሴቶች ወጣቶች እና ታዳጊዎች የእጅ ኳስ ሻምፒዮናን እንድታዘጋጅ ተመረጠች

#FastMereja I ኢትዮጵያ የ2027 የ34ኛውን የአፍሪካ ሀገራት የሴቶች ወጣቶች እና የ23ኛውን የአፍሪካ ሀገራት የሴቶች ታዳጊዎች ብሄራዊ ቡድን የእጅ ኳስ ውድድርን እንድታዘጋጅ በሙሉ ድምፅ ተመርጣለች። የአፍሪካ እጅ ኳስ ኮንፌዴሬሽን (CAHB) ከፍተኛ የውሳኔ አካል የሆነው ምክር ቤት በአንጎላ ሉዋንዳ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ነው ውሳኔውን ያሳለፈው። ሀገሪቱ ውድድሩን እንድታዘጋጅ የተመረጠችው በኢትዮጵያ እየታየ ባለው የእጅ ኳስ ስፖርት እድገት እንዲሁም ቀደም ሲል የተለያዩ ዞናዊ እና አህጉራዊ ውድድሮችን በስኬት በማስተናገዷ እንደሆነ ታውቋል።

በሉዋንዳ በተካሄደው የምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ የተሳተፉት የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን እና የምስራቅ አፍሪካ ዞን 5 ፕሬዝደንት እንዲሁም የአፍሪካ እጅ ኳስ ኮንፌዴሬሽን ምክር ቤት አባል ዶ/ር ፍትህ ወልደሰንበት፣ ኢትዮጵያ በአፍሪካ መዲና አዲስ አበባ እንግዶቿን በሙሉ ብቃትና በመልካም መስተንግዶ ለመቀበል ዝግጁ መሆኗን አብራርተዋል። የዝግጅት አቀራረቡን ተከተሎም ምክር ቤቱ አህጉራዊ ውድድሩን የማስተናገድ ሀላፊነቱን ለኢትዮጵያ ለመስጠት በሙሉ ድምፅ ወስኗል።

ይህ ከአፍሪካ እጅ ኳስ ኮንፌዴሬሽን ጋር በመተባበር የሚዘጋጀው ታላቅ አህጉራዊ ኩነት ከ15 በላይ የወጣቶች እና ከ15 በላይ የታዳጊዎች ብሄራዊ ቡድኖችን ጨምሮ ከ30 በላይ አህጉራዊ አመራሮችና ባለሙያዎችን፣ በአጠቃላይ ከ30 በላይ ቡድኖችንና ከ400 በላይ ልዑካንን ከ20 ቀናት በላይ በአዲስ አበባ ያቆያል።

ውድድሩ የሀገርን መልካም ገፅታ ከመገንባቱ ባለፈ ለሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ከፍተኛ የገበያ እድል እንደሚፈጥርና የውጭ ምንዛሪ እንደሚያስገኝ ከኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

Leave a Comment