#Fastmereja:- በኢትዮጵያ የሥነ-ውበት ዘርፍ ግንባር ቀደም ከሆኑ ተቋማት አንዱ የሆነው “ብረሽድ ባይቤቲ”(BBMI) የማሠልጠኛ ተቋም፣ በሀገሪቱ የመጀመሪያ የሆነውን ሙሉ በሙሉ በኦንላይን የሚሰጥ የሜካፕ ስልጠና በዛሬዉ እለት ይፋ አድርጓል።
የተቋሙ መስራች እና ባለቤት ወ/ሮ ቤተልሄም እስክንድር እንደተናገሩት፣ ይፋ የተደረገዉ ይህ አዲስ የኦንላይን ፕሮግራም ሰልጣኞች በማንኛውም ሰዓት እና ቦታ ሆነው በራሳቸው ምቹ ጊዜ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ተደርጎ የተዘጋጀ መሆኑን ገልፀዉ
ለአንድ ሙሉ ዓመት የሚቆየው ይህ ስልጠና በዝርዝር የተቀረጹ የቪዲዮ ትምህርቶችን፣ የተዘጋጁ ሞጁሎችን እና የሥነ-ውበት ምርቶች አጠቃቀም ሂደቶችን ያካተተ መሆኑን ገልጸዋል።
ወ/ሮ ቤተልሄም አክለዉም ሰልጣኞች በቆይታቸው በፕላትፎርሙ በጽሁፍ ጥያቄዎችን ማቅረብ የሚችሉ ከመሆኑም በላይ፣ በኦንላይን ቀጥታ (Live) ክፍለ-ጊዜዎች ከአሰልጣኞች ጋር የመወያየት ዕድል እንደሚኖራቸውና ትምህርታቸውን ሲያጠናቅቁም ኤሌክትሮኒክ ሰርተፍኬት (E-Certificate) እንደሚሰጣቸው አስረድተዋል።
ድርጅቱ ከተመሰረተ ከ8 ዓመታት በላይ ያስቆጠረዉ ይህ ተቋም በአዲስ አበባ በሚገኙት 3 ቅርንጫፎቹ እና በድሬዳዋ ቅርንጫፉ በብቁ አሰልጣኞች ታግዞ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ የሥነ-ውበት ሥልጠናዎችን በመስጠት በርካታ ባለሙያዎችን ለሥራ በማብቃት እንደሚታወቅና አሁን ደግሞ የዘመኑን የቴክኖሎጂ ዕድገት በመጠቀም ስልጠናውን ወደ ኦንላይን ፕላትፎርም ማሸጋገሩን ተገልጿል።
ተቋሙ ጥራቱን የጠበቀ ሥልጠና ከመስጠት ባለፈ ለሰልጣኞቹ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ረገድ በርካታ አዳዲስ አሰራሮችን ያስተዋወቀ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ሰልጣኞች የራሳቸውን ደንበኞች እያመጡ እንዲሠሩ የመሥሪያ ቦታ ማመቻቸት እና ለእናቶች አስተማማኝ የሕጻናት ማቆያ ማዘጋጀት ይጠቀሳሉ።
በተጨማሪም ከክልል እና ከሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች መጥተው መማር ለሚፈልጉ ሰልጣኞች የዶርምና የትራንስፖርት አገልግሎት በማመቻቸት በዘርፉ የመጀመሪያው የሆነ አሰራር መዘርጋቱን የገለፀ ሲሆን የስልጠናውን ተጠቃሚነት ለማስፋትም አቅም ለሌላቸው ሴቶች የብድር አገልግሎት የሚያገኙበት ሁኔታ መመቻቸቱ ተገልጿል።




