#Fastmereja:-የአዲስ አበባ ቴአትር እና ሲኒማ ቤቶች አስተዳደር ባለፉት ሁለት የክረምት ወራት ሲሰጥ የቆየውን ሁለገብ የስነ-ጥበብ ስልጠና በጥሩ ሁኔታ ያጠናቀቁ ከ400 በላይ ታዳጊዎችና ወጣቶችን በዛሬዉ እለት ፍላሚንጎ በሚገኘዉ የህፃናትና ወጣቶች የቴአትርና ሲኒማ አዳራሽ በደመቀ ሁኔታ አስመረቀ።
በ2018 ዓ.ም የክረምት ወቅት በተካሄደው በዚህ ሰፊ የስልጠና መርሃ-ግብር የተሳተፉት ታዳጊዎችና ወጣቶች፤ በቴአትር ጥበብ፣ በግጥም፣ በሙዚቃ፣ በድምፅ ቅላፄ፣ በዘመናዊ ዳንስ እንዲሁም በባህላዊ ውዝዋዜ ዘርፎች የንድፈ-ሐሳብና የተግባር ስልጠናዎችን ሲከታተሉ የቆዩ መሆናቸዉ ተገልጿል።
ሰልጣኞቹ በዛሬው የምረቃ መርሃ-ግብር ላይ በቆይታቸው ያገኟቸውን ዕውቀቶችና ክህሎቶች የሚያንፀባርቁ አጓጊ ጥበባዊ ስራዎቻቸውን፣ውዝዋዜዎችን፣ የሙዚቃና የተውኔት ትርኢቶችን ለታዳሚዎች አቅርበዋል።
በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ዮፍታሄ ገ/እግዚአብሄር ፣የቴአትርና ሲኒማ ቤቶች አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ፍፁም ዘገየ እንዲሁም ተመራቂ ተማሪዎች፣የተመራቂ ወላጆች እንዲሁም ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸዉ እንግዶች ተገኝተዋል።
የአዲስ አበባ የቴአትርና ሲኒማ ቤቶች አስተዳደር ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ፍፁም ዘገዬ እንደገለፁት:-በክረምቱ ወራት ከ400 በላይ ሰልጣኞችን አበቃቅቶ ወደ ኪነ-ጥበብ ዘርፍ እንዲገቡ ማድረግ መቻሉ ትልቅ ስኬት መሆኑ የተገለፀ ሲሆን ስልጠናው ወጣቶችና ታዳጊዎች የተፈጥሮ ክህሎታቸውን አውጥተው እንዲጠቀሙበትና አቅማቸውን እንዲያሳድጉ የማስቻል ትልቅ እርምጃ መሆኑን ገልፀዋል።
ይህ የኪነ-ጥበብ ስልጠና መርሃ-ግብር በክረምት ወራት ብቻ የሚከናወን ጊዜያዊ ዝግጅት ሆኖ የሚያበቃ ሳይሆን፣ በቀጣይም በቋሚነት የሚደገፍና የሚቀጥል መሆኑ ተገልፆ ይህም አዳዲስና ተስፋ ያላቸው ወጣት አርቲስቶች ሙያዊ ብቃታቸውን በማሳደግ ሀገራቸውንና ማህበረሰባቸውን በስነ-ጥበቡ ዘርፍ በብቃት እንዲያገለግሉ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ ታስቦ የተከናወነ መሆኑ ተብራርቷል።




