#FastMereja I በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በ45ኛው አጠቃላይ ዓለም አቀፍ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ላይ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የቀረበ ሪፖርት አነጋጋሪ ጉዳይ ይፋ አድርጓል። የበጀት ዓመት የሥራ ክንውንና አፈጻጸም ሪፖርት በሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ መልአከ ብርሃን ሰለሞን በቀለ ያቀረቡ ሲሆን በሪፖርቱም በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ስር አዳዲስ በሚመሰረቱ ገዳማትና አድባራት ውስጥ የስራ ሃላፊዎች ከሰበካ ጉባኤ ምክትል ሊቃነ መናብርት ጋር በመሆን ከቃለ አዋዲው መምሪያ ውጭ ህገወጥ አሰራር ሲፈጽሙ መቆየታቸው ተገልጿል።
ለዚህም ማሳያ አድርጎ ሪፖርቱ ባቀረበው መረጃ፤ በቅርብ ዓመታት ውስጥ የተመሰረተውና አሁንም በቆርቆሮ መቃኞ ደረጃ ላይ የሚገኘው የገላን ጉራ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ ፈቃድ እንዲወጡ ከተደረገ በኋላ በምክትል ሊቀመንበሩ አማካኝነት በአንድ ሌሊት 93 የጽህፈት ቤት ሠራተኞች እንዲቀጠሩ ተደርጓል።
ከነዚህም መካከል 17 የስታትስቲክስ፣ 12 የሂሳብ፣ 12 የግዢ፣ 9 ተላላኪ፣ 8 ጉዳይ አስፈጻሚ፣ 6 የእለት ገንዘብ ሰብሳቢ፣ 6 የመዝገብ ቤት ሠራተኞች እና ሌሎችም እንደሚገኙበት ተጠቅሷል። ይባስ ብሎ በአንድ የስራ መደብ ላይ የተቀጠሩት እነዚህ ሰዎች የአንድ ቤተሰብ አባላት መሆናቸው ተነግሯል።
ይህ አሰራር ለቤተክርስቲያኗ እጅግ የሚያሳዝንና ፈታኝ ከመሆኑም በላይ የምክትል ሊቃነ መናብርት የችግሩ ዋና አካል ሆነው መገኘታቸው ተመልክቷል።
በተፈጠረው ውዝግብ ምክንያት እነዚህ 93 ተከሳሾች “ያልተከፈለን ደሞዝ ደብሩና ሀገረ ስብከቱ በአንድነት እንዲከፍሉን” እና “ሀገረ ስብከቱ ደሞዝ ከፍለው ማሰራት በሚችሉ አቅም ባላቸው አድባራትና ገዳማት መድቦ እንዲያሰራን” በማለት በፍርድ ቤቶች ክስ መስርተው ይገኛሉ።
ሀገረ ስብከቱ በበኩሉ ይህ ቀደም ሲል የተፈጠረ ችግር ሲሆን ሌሎች መሰል ህገወጥ ድርጊቶችን እንዳይከተሉት ቅድመ ማስጠንቀቂያ የሚሰጥ መሆኑን አስታውቋል።
በዚህም መሰረት የደብሩ አስተዳዳሪ፣ ጸሀፊና የስራ ሃላፊዎች ከስራና ከደሞዝ እንዲሰናበቱ የተደረገ ሲሆን፣ ምክትል ሊቀመንበሩ በህግ እንዲጠየቁ እንዲሁም የደብሩ የህግ ክፍል ሃላፊ የህግ ተከታታይነት ፍቃዳቸው እንዲሻር ተደርጓል።

4 comments
እና የግል ቤተክርስቲያን መክፈት አይቻልም እንዴ?
እልል አስብሉ
ለአንድ ቤተክርስቲያን ነው ይህን ያክል ሰራተኛ በጣም ነው የሚገርመው
በሁሉም አብያተ ክርስቲያናት መፈተሽ አለበት