#FastMereja I በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ላይ በተፈጸመው ጥቃት ወደ 45 የሚጠጉ ሰዎች ሕይወታቸው ማለፉን የሚገልጹ ዘገባዎችን ተከትሎ የህንድ ማላንካራ ኦርቶዶክስ ሶሪያን ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብፁዕ አቡነ ባሴሊዮስ ማርቶማ ማቴዎስ 3ኛ ጥልቅ ኀዘናቸውን ገልጸዋል።
ብፁዕነታቸው ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ ለቤተክርስቲያኗ እና ለተጎጂ ቤተሰቦች የተሰማቸውን ጥልቅ መፅናናትና ጸሎት የላኩ ሲሆን፣ ድርጊቱንም በጽኑ ኮንነዋል። “የንጹሐን ሰዎችን ሕይወት ማጥፋት የሕይወትን ቅድስና፣ የሰብዓዊ ክብርን፣ የሃይማኖት ነፃነትን እና የአብሮ መኖር መርሆዎችን የሚጥስ አሰቃቂ ድርጊት ነው” ሲሉ ገልጸዋል።
የማላንካራ ኦርቶዶክስ ሶሪያን ቤተክርስቲያን የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ያወጣውን መግለጫ መሠረት በማድረግ እንደተገለጸው፣ ፓትሪያርኩ በሚመለከታቸው አካላት በኩል የንጹሐን ዜጎችን ደህንነት የመጠበቅ፣ ፍትሕን የማረጋገጥ እና ተጨማሪ ጥቃቶችን የመከላከል እርምጃዎች በአስቸኳይ እንዲወሰዱ አሳስበዋል።
በሁለቱ አህጉረ አብያተ ክርስቲያናት መካከል ያለው ታሪካዊ እና ሐዋርያዊ የእምነት አንድነት የጠበቀ መሆኑን ያመለከቱት ፓትሪያርኩ፣ ለተጎዱ ቤተሰቦች፣ ለቆሰሉት እና ለጠቅላላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መፅናናትንና ሰላምን ተመኝተዋል።

4 comments
????እረ
ኢየሱስ ጌታ ነው❤
የግብጽ ኮፕቲክ ና የኤርትራ ተዋህዶ ፖለቲካውን ፈርተው ዝም አሉ።
የኢትዮጵያውያኑ የት ሄዱ