banner

አርሂቡ ኢቨንትና ማርኬቲንግ ከናፍቆት ሚዲያና ማስታወቂያ ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ

#FastMereja I አርሂቡ ኢቨንትና ማርኬቲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር እና ናፍቆት ሚዲያና ማስታወቂያ ስራዎች ድርጅት በስትራቴጂክ አጋርነት አብረው ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ ዛሬ ሕዳር 8 ቀን 2019 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ብሉ በርድስ ሆቴል ተፈራረሙ። ታዋቂና ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች በተገኙበት በተካሄደው በዚህ የፊርማ ስነ-ስርዓት ላይ፤ ስምምነቱ የሁነት ዝግጅት፣ የማርኬቲንግ፣ የብራንዲንግ እና የሚዲያ ማማከር ስራዎችን በጋራ ለማከናወን ያለመ መሆኑን ከተቋማቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የአርሂቡ ኢቨንትና ማርኬቲንግ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አሸብር ጉልላት በስነ-ስርዓቱ ላይ እንደገለጹት፤ ድርጅታቸው ኢትዮጵያን በቱሪዝም፣ በገፅታ ግንባታና በኢኮኖሚ የሚያነቃቁ እንዲሁም ዓለም አቀፍ የንግድና የባህል ልውውጦችን የሚያሳልጡ ደረጃቸውን የጠበቁ ሁነቶችን ለማዘጋጀት በርካታ ፕሮጀክቶችን ነድፎ ወደ ስራ ገብቷል። ይህንን ትልም በሕዝብ ግንኙነትና በፕሮሞሽን ስራ ተደራሽ ለማድረግ ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ በዘርፉ ሰፊ ልምድ ያካበተውንና በአንጋፋዋ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ የሚመራውን ናፍቆት ሚዲያና ማስታወቂያ ስራዎችን ብቁ ሆኖ በማግኘታቸው ለአጋርነት መምረጣቸውን አብራርተዋል።

የናፍቆት ሚዲያና ማስታወቂያ ስራዎች ድርጅት መስራችና ዋና ስራ አስኪያጅ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ የኢቨንትና ማርኬቲንግ ዘርፍ ገና ያልተነካ ሰፊ ዕድል ያለው መሆኑን ጠቅሰው፣ እንደ አርሂቡ ያሉ ልምድ ባላቸው ባለሙያዎች የሚመሩ ተቋማት መቀላቀላቸው የዘርፉን ደረጃ ከፍ እንደሚያደርገው ገልጸዋል። ድርጅታቸው ከበርካታ ተቋማት መካከል ለዚህ ስትራቴጂካዊ አጋርነት በመመረጡ የተሰማቸውን ደስታ በመግለጽ፣ የተጣለባቸውን ኃላፊነት በታማኝነትና በትጋት ለመወጣት ቃል ገብተዋል።

የአርሂቡ ኢቨንትና ማርኬቲንግ የኦፕሬሽንና ኮሙኒኬሽን ኃላፊ ኢንጂነር ሳሙኤል ሰይፉ በአውሮፓ፣ በአፍሪካና በእስያ ሀገራት ያካበቱትን የሁነት ማስተባበር ተሞክሮ ከሀገር ውስጥ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማጣመር በዘርፉ ልዩነት ለመፍጠር መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል። ሁለቱ ተቋማት ከዛሬው ስምምነት በኋላ በቀጥታ ወደ ትግበራ የሚገቡ ሲሆን፣ በቀጣይም በአዲስ አበባ አዳዲስ ይዘት ያላቸው የኪነጥበብ፣ የቤተሰብ ኤግዚቢሽንና ባዛር እንዲሁም የኮርፖሬት ኩነቶችን ይፋ እንደሚያደርጉ ተገልጿል።





Leave a Comment