#Fastmereja:-ሁዳ ፕሮፐርቲስ (ሁዳ ኢንጂነሪንግ) በአዲስ አበባ 24 ቀበሌ (አደይ አበባ ስቴድየም) አካባቢ በ18 ወራት ውስጥ ገንብቶ ያጠናቀቃቸውን የመኖሪያ ቤቶች በዛሬዉ እለት ለደንበኞቹ በልዩ ሥነ-ሥርዓት አስረከበ።
በፌዴራል ማርሽ ባንድ በታጀበ ሥነ-ሥርዓት በተከናወነው የቁልፍ ርክክብ ላይ፣ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ኢንጂነር መስፍን ነገዎ፣ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ታምራት ሙሉ፣ የኢትዮጵያ ሪል ስቴት አልሚዎች ማኅበር ምክትል ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ጀበል ጀማል እንዲሁም የሁዳ መሥራችና ባለቤት ኢንጂነር ኡመር ያሲንን ጨምሮ የቤት ባለቤቶች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸዉ እንግዶች ተገኝተዋል።
የተረከቡት ቤቶች ከ90 እስከ 145 ካሬ ሜትር ስፋት ያላቸው ባለ አንድ፣ ባለ ሁለት እና ባለ ሦስት መኝታ አማራጮችን የያዙ ሲሆኑ፣ የከርሰ ምድር ውሃ፣ ትራንስፎርመር እና ጀነሬተር የተሟላላቸው መሆኑን የድርጅቱ ማርኬቲንግ ማናጀር አቶ ምስጋናው በለጠ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከ450 ሺህ እስከ 500 ሺህ የሚደርስ የቤት ፍላጎት ቢኖርም ተገንብቶ ለተጠቃሚ የሚደርሰው እጅግ አነስተኛ መሆኑን ያጠናው ሁዳ ኢንጂነሪንግ፣ በዘርፉ የሚስተዋለውን የርክክብ መዘግየት ለመቅረፍ ከዱባይና ቻይና ልምድ በመውሰድ በቴክኖሎጂ የታገዘ ፈጣን አሠራር ተግባራዊ ማድረጉን አመራሮቹ አስረድተዋል።
ከዚህም ባለፈ የግብዓት እጥረት እንዳይገጥም ብረትን ከውጭ አስመጥቶ አስቀድሞ በማዘጋጀት እና ብዙ ፕሮጀክቶችን ከመደራረብ ይልቅ አንዱን አጠናቆ ወደ ቀጣዩ በመሸጋገር ስኬታማ መሆን መቻሉ ተገልጿል።
በመኖሪያና በንግድ ሕንፃዎች ግንባታ ላይ የተሰማራው ድርጅቱ፣ ፕሮጀክቶችን ከማብዛትና ከማራዘም ይልቅ አንዱን በተያዘለት ጊዜ አጠናቆ ወደ ቀጣዩ የመሸጋገር አሠራርን እንደሚከተል ነዉ የተገለፀዉ።
በተጨማሪም በግልና በመንግሥት ተቋማት ሥራዎች ያካበተውን የምህንድስና ልምድ በራሱ ፕሮጀክቶች ላይ የሚተገብር ሲሆን፣ በዲዛይን፣ በማማከርና በቁጥጥር ዘርፍ የሚሠራ «ሂባ አርክቴክት» የተሰኘ እህት ኩባንያም አለው።
የዛሬው የቁልፍ ርክክብ ለደንበኞች የተገባውን ቃል የመፈጸም እሴትን የሚያሳይ መሆኑን ገልጸው፣ በቀጣይም በጥራትና በወቅቱ ርክክብ ላይ አተኩረው እንደሚሠሩ አስታውቀዋል።
በ2009 ዓ.ም ተመሥርቶ በ2015 ዓ.ም ወደ ሪል እስቴት ዘርፍ የገባው ሁዳ ኢንጂነሪንግ፣ ከዚህ ቀደም በቡልቡላ ሁለት ፕሮጀክቶችን አጠናቆ ያስረከበ ሲሆን በአራት ኪሎ፣ መርካቶ፣ ሀያት፣ አጣና ተራ እና ጦር ሃይሎች የተለያዩ የመኖሪያና የንግድ ሕንጻ ፕሮጀክቶችን እያከናወነ የሚገኝ ሲሆን የዚህ የቁልፍ ርክክብ ሥነ ሥርዓት የሚድያ አስተባባሪ ተወዳጅ ሚድያ እና ኮምዩኒኬሽን በጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ ተከናዉኗል።




