banner

ዳሸን ባንክ እስከ 700ሺህ ብር መሸመት የሚያስችላቸውን “ከወለድ-ነፃ ዱቤ አለ” የተሰኘ አገልግሎት አስተዋወቀ

ዳሸን ባንክ ከኤግል ላየን ቴክኖሎጂ ጋር በመተባበር ከወለድ-ነጻ የዱቤ አገልግሎት ማግኘት የሚያስችል “ከወለድ-ነጻ ዱቤ አለ” አገልግሎትን በዛሬው ዕለት ነሐሴ 10/2016 ዓ.ም በዋና መስሪያ ቤቱ አስተዋውቋል፡፡

ከወለድ-ነጻ ዱቤ አለ “IFB DubeAle” የሸሪዐህ መርሆዎችን ተከትሎ የሚሰራ አገልግሎት መሆኑ የተገለፀ ሲሆን እንደ ሽያጭ ውል የሚሰራና በደንበኛው ጥያቄ መሰረት የዱቤ አገልግሎት የሚያገኝበት አሰራር ነው ተብሏል።

ስለ አገልግሎቱ ማብራሪያ የሰጡት የዳሸን ባንክ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አስፋው ዓለሙ ተወካይ አቶ ጥላሁን ሰለሞን በባንኩ ከወለድ-ነጻ ሂሳብ ያለው ደንበኛ አገልግሎቱን መጠቀም እንደሚችል አስረድተዋል፡፡

ደንበኞች የዱቤ አለ መተግበሪያን ከፕሌይ ስቶር ወይም ከአፕ ስቶር ላይ ወደ ተንቀሳቃሽ ስልካቸው አውርደው መመዝገብ የሚችሉ ሲሆን በአቅራቢያቸው በሚገኝ የዳሸን ባንክ ቅርንጫፍ ለዱቤ አለ ማመልከት እንደሚችሉም ገልጸዋል፡፡

አቶ ጥላሁን ሰለሞን ደንበኞች በባለሙያ ታግዘው የደንበኝነት መረጃዎችን ማሟላት እና ከገቢ አቅማቸው ጋር የተገናዘበ የዱቤ ገደብዎን ማስወሰን የሚያስችል አሰራር መዘርጋቱንም አክለዋል፡፡

ባንኩ አዳዲስ አገልግሎቶችን የማስተዋወቅ ጥረቱን በመቀጠል አሁንም ከኤግል ላየን ቴክኖሎጂስ ጋር በመተባበር የቆየውን የማህበረሰባችንን የዱቤ ግብይት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እና አስተማማኝ የባንክ አሰራር በማገዝ “ከወለድ-ነጻ ዱቤ አለ” የተሰኘና ሸማቾች በዱቤ በፈለጉት ጊዜ ያሻቸውን ገዝተው ቆይተው ከወለድ-ነጻ በሆነ መንገድ መክፈል የሚችሉበትን አሰራር እንዳስተዋወቀም ተመላክቷል፡፡

ይህን አገልግሎት ለማግኘት ደንበኛው በግል እና በመንግስት መስሪያ ቤቶች ተቀጥሮ የሚሰራ ከሆነ ከሚሰራበት መስሪያ ቤት የገቢ መጠን እና የቅጥሩን ማረጋገጫ የሚገልጽ ደብዳቤ ማቅረብ ይኖርበታል።

አመልካቹ በግል ስራ የሚተዳደር ከሆነ የሚሰራውን የስራ አይነት እና ድርጅት የሚገልጹ ማስረጃዎችን ማሟላት ይጠበቅበታል።

በተጨማሪም ደምበኛው ቋሚ ንብረት ካለው እንደ ዋስትና ማስያዥያ አልያም የሶስተኛ ወገን ዋስትና ማቅረብ ይችላል። ደምበኛው በባንኩ ተቀማጭ ገንዘብ ካለው ጥሬ ገንዘብ (በዉጭ ምንዛሬ ወይም በብር) ዋስትና ማስያዝ እንደሚችልም ተብራርቷል።

ዳሸን ባንክ አሁን ላይ ባስተዋወቀው “ከወለድ ነጻ-ዱቤ አለ አገልግሎት” ደንበኞች እስከ 700,000.00 (ሰባት መቶ ሺህ ብር) ድረስ ያሻቸውን መሸመት ያስችላቸዋል፡፡

ከወለድ ነጻ ዱቤ አለ ተጠቃሚዎች ዛሬ ለገዙት በሸሪዓህ ህግ የተፈቀዱ ምርትና አገልግሎቶች ክፍያውን ወደፊት የሚከፍሉ ሲሆን አከፋፈሉም እንደ ደንበኛው ምርጫ በ3 ወር፣ በ6 ወር እና በ12 ወር ይሆናል፡፡

ዳሸን ባንክ ከዚህ ቀደም በመደበኛው የባንክ አገልግሎት ዘርፍ “ዱቤ አለ” አገልግሎትን ማስተዋወቁ ይታወሳል፡፡

Leave a Comment