banner

“ህንግጫ” የልምላሜው መልክ፤ የኮንታ አዲስ ዓመት፤

ይህ ከጳጉሜን መጨረሻ እስከ መስቀል ድረስ የሚከርመው የኮንታ ዞን አዲስ ዓመት የልምላሜ መገለጫ ነው፡፡ በኮንታዎች ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የህንግጫ በዓል የተስፋና የፍስሐ ነው።

ህዩዋ…ህዩዋ…. እንኳን አደረሳችሁ፡፡ የእኛዋ መስከረም ሙሽራ ናት፡፡ የትም ተውባ ትሰነብታለች፡፡ በሁሉም አቅጣጫ እሴትና ትውፊት ያደምቃታል፡፡ ደግሞ ቀን መስፈርና ዘመን መለካት የምድራችን ገጸ በረከት እንደኾነ ማየት ብርቅ አይደለም፡፡ አንዱ ስፍራ ኮንታ ነው፡፡

ኮንታ ህንግጫውን እያከበረ ነው፡፡ ምድሩ ለወትሮው ለምለም ነው፤ ከዚያ በላይ ሲዋብ ደግሞ ውብ ኾኖ የሚገለጽበት ሌላ ባህል ይታይበታል፡፡ ያ ህንግጫ ነው፡፡ ህንግጫ የኮንታ ብሔር ዘመን መለወጫ በዓል ነው፡፡

ኮንታ ለህንግጫ ልዩ ስፍራ ይሰጠዋል፡፡ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሻገር ከነሙሉ ክብሩ ነው፡፡ እሴቱ ሳይጎድል ውበቱ ሳይደበዝዝ እዚህ የደረሰ የማንነት መገለጫ ነው፡፡

በኮንታ ብሔር ህንግጫ የአሮጌው ዓመት መሸኛ እና የአዲሱ ዓመት መጀመሪያ ወይም መሸጋገሪያ በዓል ነው፡፡ የአብሮነት፣ የኅብረትና የፍቅር በዓል በመኾኑ ልዩ ቦታ ይሰጠዋል፡፡ ወዳጅ ዘመድ ይጠያየቅበታል፡፡

የቃሉ ትርጓሜ ያማረ፣ ያጌጠ፣ የለመለመ ማለት ሲሆን ዐደይ አበቦች ፈክተው ምድር ስታጌጥ የኮንታ ውብ ቀዬ ደማቅ ቀለም ለብሶ ከቀደመ ውበት በላይ ሲዋብ ይከበራል፡፡

እንደ ባህሉ ትውፊት ህንግጫ ከጳጉሜን የመጨረሻዋ ቀን እስከ መስከረም 30 ድረስ ደምቆ ይቆያል፡፡ የመስቀልን በዓል የህንግጫ አካል ነው፡፡ ከቤት እስከ ደጃፍ አካባቢ ይጸዳል፡፡ ከአዲሱ ዓመት የሚሻገር እድፍና ጉድፍ ይጠረጋል፡፡ ምድር ትዋባለች፡፡

ህንግጫ ከ12 ዓይነት በላይ የኾነው የኮንታ ባህላዊ ምግብ ተዘጋጅቶ የሚቀርብበት የባህል አውድም ነው፡፡ የዘመን መለወጫ በዓል ማብሰሪያ እሳት የሚወጣው ጳጉሜን የመጨረሻዋ ቀን ነው፡፡

በህንግጫ በዓል ያለው ለሌለው አካፍሎ የሚበላበት፣ ደሃ ከሀብታም የማይለይበት የወል በዓል ነው፡፡ የአብሮነት ተምሳሌት፤ እንኳን ለህንግጫ በዓል በሠላም አደረሳችሁ፡፡

ህዩዋ ህዩዋ ህንግጫው፤
#Balager_Tube



1 comment

Mėsfìņ Đmű August 28, 2024 - 10:28 am

በ #ጉራጌ ደሞ #እንጊጫ ተብሎ ይከበራል ውብ ባህል 🙏

Reply

Leave a Comment