banner

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን የዳሰነች ማህበረሰብ ከባድ የጎርፍ አደጋ ውድመት እና ኪሳራ እያስተናገደ ይገኛል።

በዳሰነች ወረዳ የሚገኙ 40 ቀበሌዎች ውስጥ 80% የሚሆኑ ቀበሌዎች በውሃ ተውጠዋል እንዲሁም የተለያዩ የማህበረሰብ ልማቶች፤ የመንግስት ተቋሞች፤ መንገዶች፤ የግጦሽ መሬቶች፤ ከብቶች፤ የእርሻ ማሳዎች በጠቅላላ መሠረተ ልማቶች ወድመዋል። ማህበረሰቡም ተፈናቅለው በተለያዩ መጠለያዎች ውስጥ በመጠለል ይገኛሉ።

ይህ በእንዲህ እንዳሌ በዳሰነች ወረዳ የኦሞ ወንዙ በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ እና መደበኛ የመፍሰሻ አቅጣጫውን ለቆ በመውጣቱ እና የቱርካና ሀይቅ መደበኛ ይዞታውን በማስፋቱ የዳሰነች ወረዳ ኦሞራቴ ከተማ ላይ ከፍተኛ ስጋት እና ጭንቀት በማህበረሰቡ ላይ ተፈጥሯል።

በተጨማሪም የወረዳው መንግስት የኦሞራቴ ከተማን ለማዳን በኦሞ ወንዝ ላይ እየተሰሩ ያሉ የጎርፍ መከላከያ የአፈር ግድቦች በወንዙ ውሃ በመሰበራቸው ውሃው ወደ ኦሞራቴ ከተማ እየፈሰሰ ይገኛል።

የጎርፍ አደጋውን ተከትሎ የሚደርሱ ጉዳቶችን ለመቀነስ የዳሰነች ወረዳ መንግስት እና የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በጋራ ከአከባቢው ማህበረሰብ ጋር ርብርብ ቢያደረግም ከአቅም በላይ መሆኑ ተገልጿል።
“የጎርፍ አደጋ የቅድመ መከላከል ሥራው ከአቅማችን በላይ ሆኗል የሚመለከታቸው አካላት ድጋፍ ያድርጉ” አቶ ታደለ ሀቴ የዳሰነች ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ

ኦሞራቴ ነሀሴ 18 ቀን 2016 የኦሞ ወንዝ ሞልቶ በተከሰተ የጎርፍ አደጋ እና የቱርካና ሀይቅ መደበኛ ይዞታውን በማስፋቱ በአከባቢው የተከሰተውን የጎርፍ አደጋ የቅድመ መከላከል ሥራ ከአቅም በላይ መሆኑን አስመልክቶ የዳሰነች ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደለ ሀቴ መግለጫ ሰጥተዋል።

የጎርፍ ቅድመ መከላከል ሥራው በወረዳ፣ በዞን እና ከኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ጋር በጋራ ትብብር ሲሰራ መቆየቱን ዋና አስተዳዳሪው ገልፀው ውሃው ሰብሮ በመጣባቸው በተለያዩ አከባቢዎች ጊዜያው መፍትሄ ለመስጠት በአፈር የመገደብ ሥራ መሰራቱን ተናግረዋል።

ጊዜያዊ መፍትሄ ለመስጠት በአፈር የተገደቡ አከባቢዎች የውሃው ግፊት ከፍተኛ በመሆኑ ግድቦቹ እየተሰበሩ በአከባቢው ከፍተኛ ስጋት መፈጠሩን አቶ ታደለ ሀቴ ገልፀው በወረዳው ዋና ከተማ ኦሞራቴ ላይ በከፍተኛ ሁኔታ በውሃ የመጥለቅለቅ አደጋ መደቀኑን ተናግረው 11 ደረቃማ ተብለው የተለዩ የመጠለያ ጣቢያዎች በውሃ እየተከበቡ መሆኑን ዋና አስተዳዳሪው ተናግረዋል።

የጎርፍ አደጋ የቅድመ መከላከል ሥራው ከአቅም በላይ በመሆኑ የሚመለከታቸው አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉ አቶ ታደለ ሀቴ ጥሪ አቅርበዋል።





Leave a Comment