banner

በኦሮሚያ መንግስት ሙሉ ወጪ በትግራይ የተገነባው ትምህርት ቤት ተጠናቆ ለአገልግሎት ዝግጁ ሆነ

በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በ179 ሚሊዮን ብር ወጪ በትግራይ ክልል ሽሬ እንዳስላሴ ከተማ የተገነባው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታው ተጠናቆ ለአገልግሎት መዘጋጀቱ ተገለጸ።

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የሽሬ እንዳስላሴ ከተማ ትምህርት ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ገብረመድህን ወልደጊዮርጊስ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ሙሉ ወጪ በከተማዋ ሲገነባ የቆየው ትምህርት ቤቱ በአዲሱ ዓመት አገልግሎት ይጀምራል።

በሁለት ፈረቃ 2 ሺህ 160 ተማሪዎችን የመቀበል አቅም ያለው ትምህርት ቤቱ የመማርያ ክፍሎችን እንዲሁም ለተለያዩ አገልግሎት የሚውሉ ክፍሎችን ያካተተ መሆኑን ኃላፊው ገልፀዋል።

የህንፃ ብሎኮቹ ዲጂታል ቤተ መጻሕፍት፣ ላቦራቶሪ፣ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ማዕከል፣ ዎርክ ሾፕ፣ የስብሰባ አዳራሽና መለስተኛ ክሊኒክን ያካተተ እንደሆነም አስረድተዋል።

የፕሮጀክቱ ስራ አስኪያጅ አቶ ገለታ ጫላ በበኩላቸው፤ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቱ በአራት ነጥብ ሁለት ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ መሆኑንና በ10 ወራት ውስጥ ተገንብቶ ዘንድሮ ትምህርት ዘመን ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል።

ዘገባው የአዲስ ስታንዳርድ ነው።

Leave a Comment