banner

ሀሰተኛ ሰነዶችን በማዘጋጀት፣ ህገ-ወጥ ገንዘብ በማተምና በህገ-ወጥ መንገድ ገንዘብ ከቦታ ወደ ቦታ በማዘዋወር የተጠረጠሩ ግለሰ

ሀሰተኛ ሰነዶችን በማዘጋጀት፣ ህገ-ወጥ ገንዘብ በማተምና በህገ-ወጥ መንገድ ገንዘብ ከቦታ ወደ ቦታ በማዘዋወር የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ።

የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ሀላፊ የተከበሩ አቶ አለማየሁ ጢሞቴዎስ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ በክልሉ ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች በነፃነት የመንቀሳቀስ ሀብት የማፍራት እና በሰላም ወጥቶ የመግባት ነፃነት እንዲኖራቸው የክልሉ መንግስት ስለ አስተማማኝ ሰላም መስፈን ሌት ተቀን ተግቶ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

በክልሉ በተሰራው የኦፕሬሽን ስራ ፎርጂድ ካርታ፣ ቼክ፣ የትምህርት ማስረጃ፣ የባንክ ቤት ቼኮች፣ የስራ ቅጥርና ስንብት፣ ሀሰተኛ የብር ኖቶች፣ የተለያዩ ሀሰተኛ መታወቂያዎችና ሌሎች ሰነዶችንም በማዘጋጀት ሲያሰራጩ የነበሩ ተጠርጣሪዎች ከሚሰሩበት ቁሳቁስ ጋር በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተናግረዋል።

በተሰራው የኦፕሬሽን ስራም መነሻውን አርሲ ዞን በማድረግ በሎካ አባያ ወረዳ አቋርጦ ለፀረ ሰላም ሀይሎች ሊደርስ በሰሌዳ ቁጥር ኮድ3-027122 በሆነ አይሱዙ መኪና ተጭኖ ሲጓዝ የነበረ 18 ኩንታል አደንዛዥ እፅ ከነ ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር መዋሉን ገልፀዋል።

ሀላፊው አክለውም ከሀገር ውስጥ የተለያዮ የከበሩ ማዕድናትን ወደ ጎረቤት ሀገራት ለማሸጋገር ሲያጓጉዙ የነበሩ ተጠርጣሪዎች ከነ ማዕድናቱ በቁጥጥር ስር ማዋል መቻሉን የገለፁት ሀላፊው በህገ-ወጥ መንገድ የተከማቸ የውጭ ሀገራት ገንዘብም ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ በቁጥጥር ስር ውሎ ወደ ባንክ ገቢ መደረጉን ገልፀዋል።

ባጠቃላይ በተጠቀሱት ወንጀሎች ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉት ዘጠኝ ተጠርጣሪዎች ሲሆኑ በተጠርጣሪዎቹ ላይም ምርመራ እየተጣራ መሆኑንም አስታውቀዋል።

ተጠርጣሪዎቹን በቁጥጥር ስር ለማዋል የህብረተሰቡ ሚና ከፍተኛ ነበር ያሉት ሀላፊው ወደፊትም የክልሉን ሰላም ለማፅናት በሚደረገው ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ህብረተሰቡ የተለመደውን ትብብር እንዲያደርግ ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።





Leave a Comment