banner

ከገበያ የተሰረቀ አህያ በባለቤቱ በር ሲያልፍ ጊቢ ውስጥ በመግባት አልወጣም በማለቱ አህያውን የሰረቀው ግለሰብ በቁጥጥር ስር ዋ

ከገበያ የተሰረቀ አህያ በባለቤቱ በር ሲያልፍ ጊቢ ውስጥ በመግባት አልወጣም በማለቱ አህያውን የሰረቀው ግለሰብ በቁጥጥር ስር ዋለ

ከገበያ ውስጥ ከታሰረበት የተሰረቀ አህያ ከባለቤቱ በር ሲያልፍ ከጊቢው በመግባት ተመልሶ አልወጣም በማለቱ የአህያው ሰራቂ በቁጥጥር ስር ውሎ በእስራት መቀጣቱ የባሌ ዞን ፖሊስ አስታወቀ።

በባሌ ዞን በሀረና ቡሉቅ ወረዳ መልከሀራባ በተባለ አካባቢ ከገበያ ውስጥ የተሰረቀው አህያ በባለቤቶቹ ጊቢ ሲያልፍ ተመልሶ በመግባት አልወጣም በማለቱ የአህያው ሰራቂ በቁጥጥር ስር ውሎ በእስራት መቀጣቱን የወረዳው ፖሊስ አስታውቋል።

የሀረና ቡልቅ ወረዳ ፖሊስ ፅህፈት ቤት የወንጀል ምርመራ ክፍል መርማሪ ረዳት ኢንስፔክተር ጉዮ ጭቁሩ እንደገለፁት ተከሳሽ አሚን ሀሰን ሁሰኔ የተባለው ግለሰብ ከገበያ ውስጥ ታስሮ የነበረ የአቶ አብዱል ሁሴን አህያ ከታሰረበት በመውሰድ ወደ መኖሪያ አካባቢው ይዞት በመሄድ ለሳምንታት እሱ ዘንድ እንዳስቀመጠው ገልፀዋል።

ከሳምንታት ቆይታ በኋላም ተከሳሽ ከገበያ ፈቶ የወሰደውን አህያ በመንዳት አንጋቱ የተባለ ገበያ ለመሸጥ እየነዳ እያለ ከገበያ የተወሰደው አህያም የአቶ አብዱላሂ ሁሴን ጊቢ ሲደርስ በረት ውስጥ በመግባት አልወጣም በማለቱ በተፈጠረ የግርግር ድምፅ አህያ የጠፋባቸው ባለቤት ወተው ሲመለከቱ ከሣምንታት በኋላ አህያው ገቢያቸው ውስጥ በመገኘቱ ወዲያውኑ ጉዳዩን ለፀጥታ አካላት በማሳወቅ ተከሣሹ በቁጥጥር ስር ሊውል ችሏል።

የአህያው ባለቤት አቶ አብዱላሂ ሀሰን ቀደም ሲል ለአካባቢያቸው የፀጥታ አካላት ከሳምንት በፊት አህያቸው ከገበያ ውስጥ እንደተሠረቀባቸው በማመልከታቸው የፀጥታ አካላት ወዲያውኑ አህያውን ከገበያ ፈቶ በመውሰድ ሊሸጥ የሞከረውን ግለሰብ በቁጥጥር ስር አውለው ለፖሊስ ማስረከባቸው ገልፀዋል። ፖሊስም እጅ ከፍንጅ የተያዘው ግለሰብ ላይ በአፋጣኝ የምርመራ መዝገብ በተያዘው አህያ ኤግዚቢትነት እና በሰው ማስረጃ በማጠናከር ለአቃቤ ህግ መላኩን ገልፀዋል።

አቃቤ ህግም ከ ፖሊስ የተላከለትን መዝገብ ተመልክቶ በአፋጣኝ ችሎት ክስ በመመስረት የክስ መዝገቡ ለሀረና ቡሉቅ ወረዳ ፍርድ ቤት መላኩን ተናግረዋል።የሀረና ወረዳ ፍርድ ቤትም መስከረም 15 ቀን 2017 በዋለው ችሎት ተከሳሽ አሚን ሀሰን ሁሴን ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ በ ሁለት አመት ከ አራት ወር እስራት እንዲቀጣ የተወሰነበት መሆኑን ረዳት ኢኒስፔክተር ጉዮ ጭቁሩ ለብስራት ጨምረው ገልፀዋል።ከገበያ የተሰረቀው አህያ ባለቤቶቹ ጊቢ በመግባት አልወጣም በማለት የሰረቀውን ግለሰብ እጅ ከፍንጅ በማስያዙ በርካቶችን አስገርሟል።

Via: ዳጉ ጆርናል

Leave a Comment