በአፈንዲ ሙተቂ
—–
ስለኢሬቻ (ኢሬሳ) የተጻፈ ጽሑፍ በዚህ ግድግዳ ላይ ደጋግሜ ለጥፌአለሁ። በጽሑፉ እንደገለጽኩት “ኢሬቻ ባዕድ አምልኮ ነው” የሚባለው ነገር በጣም ስሕተትና ፎርጅድ ወሬ ነው። ኢሬሳን “ባዕድ አምልኮ” በሚባለው ሐረግ መግለጽ ለምን እንደተፈለገም አይገባኝም። ባዕድ አምልኮ የሚባለው ለጂንኒ፣ ለጋኔን ወይንም ለሸይጣን መስገድ ነው? ለጂንኒ የደም መስዋእት ማቅረብ ማለት ነው? እንደዚያ ከሆነ ኢሬሳ ከነዚህ ድርጊቶች ጋር ግንኙነት የለውም።
——
እኔ ስለኢሬሳ (ኢሬቻ) የተማርኩት በቢሾፍቱ ሳይሆን በተወለድኩበት ምድር ከሚኖሩት የሀረርጌ ሽማግሌዎች አንደበት ነው። ሽማግሌዎች እንዳስተማሩን የሀረርጌ ኦሮሞዎች የእስልምና ሃይማኖትን ከመቀበላቸው በፊት እንደ ሌሎች ኦሮሞዎች ኢሬሳን በየዓመቱ ያከብሩት ነበር። በዓሉ የሚከበረው በክረምቱ ዝናቡን አዝንቦ ለሕዝቡ የእርሻ ምርትን፣ ለከብቶች ለምለም ሳርንና ለቀጣዩ ዓመት የሚሆን የ”ሃያ” ውሃን ለሰጠው አንድዬ አምላክ (Waaq Tokkichaa) ምስጋና ለማቅረብ ነው። በበዓሉ ላይ የሚመሰገነው ዋቃ፣ የሚለመነውም ዋቃ፣ ቃል ኪዳን የሚያዘውም በዋቃ ነው። አምልኮ ካለም የሚመለከው “ዋቃ” ብቻ ነው።
ከዚህ ባለፈ አዲሱ ዓመት በመልካምነቱ ይዘልቅ ዘንድ ደግነትን የሚያሳዩና ወንድማማችነትን የሚያጎለብቱ ተግባራት በክብረ በዓሉ ላይ ይፈጸማሉ። ለምሳሌ የተጣሉ ሰዎች ይቅር ይባባላሉ። ገንዘቡን ለሌሎች ያበደረ ሰውም የተበዳሪዎችን ዕዳ ይሰርዝላቸዋል። ወዘተ…ኢሬሳ የደስታ በዓል ስለሆነ በተዋቡ ልብሶች መድመቅና ማጌጥ የክብረ በዓሉ ወግ ነው።
በአጭሩ ኢሬሳ (ኢሬቻ) ለዋቃ የምስጋና ማቅረቢያ በዓል ነው። ነገሩን ከስረ መሠረቱ ማወቅ የሚፈልግ ሰው “ቦረና እና በሬንቱ” በተሰኘው መጽሐፌ ያቀረብኩትን ሰፊ ወግ ማንበብ ይችላል።
——-
ከላይ እንደገለጽኩት ኢሬሳ ባዕድ አምልኮ አይደለም። ከባዕድ አምልኮ ጋር የሚያገናኘው ነገርም የለም። ይልቅ አከራካሪው ነገር “ኢሬሳ ባህል ነው ወይስ ሃይማኖታዊ በዓል ነው?” የሚለው ነው። እኔ በመጽሐፌ ስለኢሬሳ የጻፍኩት “የጥንቱ የኦሮሞ ሕዝብ እምነት የሆነው የዋቄፈንና ሃይማኖታዊ በዓል ነው” በማለት ነው። እውነቱም ይኸው ነው። በዚህ ረገድ ከወዳጄ ጋዲሳ ሆማ ( Gadissa Homa ) እና ከዶክተር ገመቹ መገርሳ ጋር ተመሳሳይ አቋም አለኝ። የዘመናችን የዋቄፈንና እምነት አማኞችም ሆነ ሙስሊም እና ክርስቲያን የሆኑ ሽማግሌዎቻችንም ተመሳሳይ ነገር ነው የሚናገሩት።
እኔ ሙስሊም ስለሆንኩ በዓሉን ከሚያከብሩት አይደለሁም። ይሁንና በዓሉን ከሚያከብሩት ጋር ምንም ዓይነት ግጭት የለኝም።
——
“ኢሬሳ’ን ለሚያከብሩት ወገኖቻችን በሙሉ መልካም በዓል እንዲሆንላቸው እንደመኛለን። በዓሉን የማታከብሩ አንዳንድ ሱሰኞች ደግሞ “ባዕድ አምልኮ ነው” እያላችሁ ነገር መፈለግንና የሰውን መብት መዳፈርን እንድትተውት መልእክታችንን እናሰተላልፋለን።
سلام
ሰላም።
Nagayaan Jiraadhaa.
