banner

የቦሌ ሆምስ – ጎሮ የመንገድ ፕሮጀክት ግንባታ 85 በመቶ ተከናውኗል ተባለ።

በአዲስ አበባ ከተማ ከቦሌ ብራስ የቀለበት መንገድ መጋጠሚያ ጀምሮ በቦሌ ኤርፖርት በኩል ወደ ጎሮ አይ.ሲ.ቲ ፓርክ እየተገነባ የሚገኘው የመንገድ ፕሮጀክት 85 በመቶ አፈፃፀም ላይ ደርሷል፡፡

ይህ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት በአጠቃላይ 4.9 ኪሎ ሜትር ርዝመትና 60 ሜትር የጎን ስፋት ያለው ሲሆን፣ ከ1.6 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ የውል ዋጋ እየተገነባ ይገኛል፡፡

ቀደም ሲል ከቦሌ ብራስ የቀለበት መንገድ መጋጠሚያ ጀምሮ 1.3 ኪ.ሜ የሚሆነው የመንገዱ ክፍል የአስፋልት ንጣፍ ስራ ተከናውኖ በከፊል አገልግሎት እየሰጠ መሆኑም ይታወቃል፡፡

አሁን ላይ ከቦሌ ጉምሩክ ጀምሮ እስከ ጎሮ ባለው ቀሪ የመንገድ ፕሮጀክቱ ክፍል በመከናወን ላይ የሚገኘው የሰብ ቤዝ፣ ከርቭ ስቶን፣ የድልድይ፣ የከልቨርት ቦክስና የድጋፍ ግንብ ስራ ወደ ማጠናቀቂያ ምዕራፍ ተሸጋግሯል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ከቦሌ ኤርፖርት ካርጎ ተርሚናል ፊት ለፊት ወደ ገርጂ ሮባ ዳቦ በሚያስወጣው እና 600 ሜትር ርዝመት ባለው የመንገድ ፕሮጀክቱ ሌላው ክፍል፣ የከርቭ ስቶን እና የሰብ ቤዝ ስራ በከፊል ተጠናቆ ለትራፊክ እንቅስቃሴ ክፍት ተደርጓል፡፡

በቅርቡም ቀሪ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቱን የአስፋልት፣ የእግረኛና ቀሪ የስትራክቸር ስራዎች ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል፡፡

የመንገድ ፕሮጀክቱ ግንባታ ሲጠናቀቅ ከቱሉ ዲምቱ የክፍያ መንገድ አቅጣጫ በጎሮ በኩል ወደ መሃል አዲስ አበባ ለሚገቡ ተሽከርካሪዎች፣ እንዲሁም ከአይ.ሲ.ቲ ፓርክ ወደ አራብሳ እየተገነባ ከሚገኘው ሌላኛው የመንገድ ፕሮጀክት ጋር ተሳስሮ አቋራጭና አማራጭ መንገድ ሆኖ የሚያገለገል ይሆናል፡፡

1 comment

Edom Mekonnen October 20, 2024 - 11:45 am

ደና አቋራጭ ነበር ግን ዘጉት አረ ባካቹ ክፈቱልን የዘጉት ፎቶ ለማንሳት ከሆነ አነሳቹ አይደል ክፈቱልን

Reply

Leave a Comment