banner

የአዲስ ኪዳን ግሪክኛ – አማርኛ መዝገበ ቃላት ዝግጅት ተጠናቆ ሊመረቅ ነው።

#FastMereja I በአቶ ብሉጽ ፍትዊ የተዘጋጀውና የብዙ ዓመታት ድካምና ጥረት ውጤት የኾነው የአዲስ ኪዳን ግሪክኛ – አማርኛ መዝገበ ቃላት ሥራ ተጠናቅቆ ለኅትመት መብቃቱ ተገለፀ። አቶ ብሉጽ ለዓመታት የደከሙበት የመዝገበ ቃላት ሥራ የኅትመት ብርሃን ያይ ዘንድ፣ ለገርጂ አማኑኤል ኅብረት ቤተ ክርስቲያን በዐደራ በሰጡት መሠረት፣ ተገቢውን የአርትኦትና የእርማት ኺደት በመከተል ለማሳተም መቻሉ ተገልጿል።

መዝገበ ቃላቱ ከ5,000 በላይ የዐዲስ ኪዳን ግሪክ ቃላትን በቀጥታ ወደ ዐማርኛ የሚተረጕም ሲኾን፣ ለእያንዳንዱ የቃል ፍቺም ተዛማጅ የዐዲስ ኪዳን ክፍሎችን ያጣቅሳል ተብሏል። አያይዞም የግሪክ አቡጊዳ፣ ሙዳየ ቃላትና አጠቃላይ የግሪክ ቋንቋን ታሪካዊ ዳራ ያቀርባል። ይህም በኢትዮጵያ የመዝገበ ቃላት ኅትመት ታሪክ ውስጥ በዐይነቱ ልዩና የመጀመሪያ እንደሚያደርገው ነው የተገለፀው።

ይህ ታሪካዊ ሥራ “ዐደራ” የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን፣ ሥራውም የኅትመት ብርሃን እንዲያገኝ አቶ ብሉጽ ለገርጂ አማኑኤል ኅብረት ቤተ ክርስቲያን በዐደራ ሰጥተዋል። ቤተ ክርስቲያኒቱም ዐደራውን ተወጥታ የምረቃ መርሓ ግብሩ ሰኞ ጥቅምት 25 ቀን 2017 ዓ.ም. የቤተ እምነት መሪዎች፣ የቤተ ክርስቲያን መጋቢዎች፣ የነገረ መለኮትና ልዩ ልዩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አመራሮች እንዲሁም የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ተወካዮችን ጨምሮ ከ1,500 በላይ እንግዶች በተገኙበት በስካይላይት ሆቴል በልዩ ኹኔታ ይከናወናል ተብሏል።

በዕለቱ የዝማሬ አምልኮ፣ የቃለ እግዚአብሔር ስብከት እና የፓናል ውይይት የሚካኼድ ሲኾን፣ ስለ መዝገበ ቃላቱ አጠቃላይ የዝግጅት ኺደት የሚያስረዳ ዐጭር ዘጋቢ ፊልም ለዕይታ ይቀርባል። በተጨማሪም የተለያዩ የቤተ እምነትና ተቋማት መሪዎች ንግግር የሚያደርጉ ሲኾን፣ ለሚመለከታቸው አካላት የምስጋና ዕውቅና ይሰጣል።





1 comment

Eto-kranyo Eto-Kranyo October 25, 2024 - 9:34 am

ከመፅሀፍ ቅዱስ ውጪ ሁሉም ተረት ተረት ነው ይሉ ነበር ሀሳብ ቀይረው ነው!?

Reply

Leave a Comment