በደቡብ ምዕራብ ክልል ካፋ ዞን ጨታ ወረዳ ለልማት በሚል መምህራን “ያለፈቃዳቸው” የአንድ ወር ደሞዛቸው ለመዋጮ እንደተቆረጣባቸው ገልጸዋል።
መምህራኑ “ለገጠር መንገድ ግንባታ” ይውላል የተባለ እና በአንድ ዓመት የሚቆረጥ የአንድ ወር ደሞዝ ስምምነት ላይ ሳይደርሱ “በጅምላ” እና “በማን አለብኝነት” መቆረጡን ይናገራሉ።
“ከ50 በመቶ በላይ [የመንግሥት ሠራተኞች] ደገፉት ስለተባለ በጅምላ ይቆረጣል” ተብሎ መወሰኑን የተናገሩ አንድ የአንደኛ ደረጃ መምህር፤ ፈቃደኝነታቸው እና አቅማቸው ውሳኔው ላይ ሚዛን እንዳልደፋ ተናግረዋል።
“መምህራን የልማት ተቋዳሽ አይደሉም ሳይሆን፤ አቅማችን የማይፈቅደውን አትጠይቁን ነው እያልን ያለው” ሲሉ አንድ መምህር ምሬታቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።
መዋጮው መምህራን ላይ ብቻ ያነጣጠረ እንዳልሆነ የጠቆሙ ሌላ መምህር አነስተኛ ገቢያችንን እና የኑሮ ጫናን አገናዝቦ “በአቅማችን ይሁን” የሚል ሀሳብ እንዳለ ተናግረዋል።
“የአራት ሺህ ብር ደሞዝተኛ ነኝ። አራት ሺህዋን ብር ከምትወስዱብኝ እባካችሁ 1500 ብር በእጄ ልስጣችሁ [ብዬ] ለመንኩ” ብለዋል የወረዳው ባሺ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር።
“እርዳታ ነው፤ አስተዋጽኦ ነው፤ ለልማት አሻራችሁን አሳርፉ ነው የሚባለው። ሰው በቻለው ነው። . . . የሚችል ነው የሚደግፈው” ሲሉ በአቅማቸው ለማዋጣት ጥያቄ ቢያቀርቡም የወረዳው አስተዳዳሪዎች ግን “የአንድ ወር ደሞዝ ሙሉ ካልሆነ አይቀበሉም” ብለዋል።
የጥቅምት ወር ደሞዝ የተቆረጠባቸው መምህራን አቤቱታ ለማቅረብ ወደ መንግሥት ተቋማት ሲያቀኑ እንግልት እንደደረሳቸው አንድ መምህር ሲናገገሩ፤ ሌላ መምህር ደግሞ “በፖሊስ ታፍነን ነበር” ብለዋል።
“ሰርቆ እንደሄደ ሰው [በፖሊስ] ታጅበን ነው የሄድነው” ሲሉ አንድ መምህር ክስተቱን ለቢቢሲ ገልጸዋል።
በወረዳው ለሁለት ቀናት ያህል ትምህርት ተቋርጦ እንደነበር የተናገሩት መምህራን፣ ከዞኑ አስተዳደር ገንዘባቸው እንደሚመለስላቸው ስለተነገራቸው ማስተማር መጀመራቸውን ተናግረዋል።
“መምህር በመሆኔ በጣም ነው ተቆጨሁት። መምህር ከወር ደሞዝ ውጪ የሚያገኘው አንዳች ነገር የለም። አዲሱ ክልል ከተመሠረተ ወዲህ እስከ 50 ቀን ድረስ ቆይቶ ነው ደሞዛችን የሚከፈለን። ይህን ታግሰን፤ ሆድ እና ጀርባችን ተጣብቆ፣ ስቃይ አይተን ደግሞ ይሄ ደሞዝ ሲቆረጥ፤ መብታችንን ማንም ሳያስከብርልን ሲቀር. . . መምህር በመሆኔ በጣም አዝናለሁ” ሲሉ በምሬት ያሉበትን ሁኔታ ገልጸዋል።
ዘገባው የቢቢሲ አማርኛ ነው

10 comments
ለማን አቤትት ይባል
ያሳዝናል። ድንጋይ የመታውን ሳር ያደማዋል!!!
ወደ ሰማይ መናገር እንጂ በምድር ላይ ሰሚ የለም
የ6 አመቱ የለውጥ ጉዞ የብልፅግናችን ትሩፋት ድምር ውጤት
በአሁኑ ግዜ መምህር የምሆን ሰው የተረገመ ነው።
ልማት ከሰባዊነት በልጦ መታየት ከጀመረ ሰንበትበት ብሏል እኮ ወገን
ከባድ ነው
እፉፉ ያሳዝናል
DON’T SAY LIKE THIS BECAUSE TOMORROW WILL BE NICE STAY HUMBLE AND PATIENT
Sad truth