banner

የግድያ ወንጀል እንደፈፀመች አምና በፖሊስ ቁጥጥር ሥር በነበረች የቤት ሰራተኛ ላይ በተደረገው ጥልቅ እውነትን የማፈላለግ የምር

የግድያ ወንጀል እንደፈፀመች አምና በፖሊስ ቁጥጥር ሥር በነበረች የቤት ሰራተኛ ላይ በተደረገው ጥልቅ እውነትን የማፈላለግ የምርመራ ሥራ የወንጀሉ ተጠርጣሪ አሰሪዋ ሆና እንደተገኘች የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፤ ምርመራው ቀጥሏል፡፡
****
ህፃን ሰላማዊት አስፋው የ12 ዓመት ታዳጊ ስትሆን ነዋሪነቷም በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ሐድያ ዞን ነው ። በሐምሌ ወር 2016 ዓ.ም የአጎቷ ልጅ የሆነችው ወ/ሮ ዓለምፀሐይ ስላሴ ለህፃኗ ወላጆቿ እያስተማረች ልታሳድጋት ቃል በመግባት በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 ልዩ ቦታው አለም ባንክ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ መኖሪያ ቤቷ ይዛት በመምጣት መኖር ትጀምራለች፡፡

መስከረም 3ቀን 2017 ዓ.ም ከቀኑ 5 ሰአት ሲሆን ለግዜው የፀቡ መነሻ ባልታወቀ ምክንያት ህፃን ሰላማዊት አስፋው ህይወቷ ያልፋል፡፡ ህፃኗን እያስተማረች ልታሳድጋት ያመጣቻች ተጠርጣሪ ታዳጊዋን የተለያየ የሰውነት ክፍሏን በእንጨት በመደብደብ ከ20 ቦታ በላይ ጉዳት በማድረስ እና አንገቷን በማነቅ ህይወቷ እንዲያልፍ ማድረጓን የምርመራ መዝገቡ ያስረዳል፡፡

በህፃኗ ህልፈተ-ህይወት ተጠያቂ ላለመሆን ያሰቡት ተጠርጣሪዋ ግለሰብ ከባለቤቷ ጋር በመነጋገር በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ በቤት ሰራተኝነት ተቀጥራ በመስራት ላይ የምትገኝ የ17 ዓመት ዕድሜ ያላት ተስፋነሽ ጀባኔን ህፃኗን በድንገት እንደገደለቻት ለፖሊስ ቃል እንድትሰጥና ለውለታዋም ደሞዟን በእጥፍ እንደሚጨምሩላት በተለያዩ መደለያዎች በማሳመን߹ በወንጀሉም ጉዳይ ጠበቃ እንደሚቀጥሩላት ካሳመኗት በኋላ ለፖሊስ በሰጠችው ቃል የወንጀል ድርጊቱን እንደፈፀመች የሚገልፅ ነበር፡፡

ሆኖም ፖሊስ የተስፋነሽ ጀባኔን ቃል መነሻ በማድረግ የምርመራ ስራውን በማስፋት ሂደት ለጊዜው ተጠርጣሪ የሆነችው የቤት ሰራተኛ እኔ ነኝ የገደልኳት ብትልም አንዳንድ አጠራጣሪ ነገሮች መኖራቸውን የደረሰበት ፖሊስ ባደረገው ጥልቅ እውነትን የማፈላለግ የምርመራ ሥራ የወንጀል ድርጊቱን የቤት ሰራተኛዋ እንዳልፈፀመች እና ልታሳድግ እና ልታስተምራት ባመጣቻት ግለሰብ በደረሰባት ድብደባ ህፃን ሰላማዊት አሰፋ ህይወቷ እንዳለፈ ይደርስበታል።

የምርመራ ሂደቱ ቀጥሎ ተጠርጣሪዋ ግለሰብም የወንጀል ድርጊቱን መፈፀሟን አምና በመኖሪያ ቤቷ ድርጊቱን እንዴት እንደፈፀመች መርታ ማሳየቷን የአዲስ አበባ ፓሊስ አስታውቋል። ተጠርጣሪ ግለሰቧና ባለቤቷ ጉዳያቸውን በማረሚያ ቤት ሆነው እንዲከታተሉ ፍ/ቤቱ እንዳዘዘ ፖሊስ ጨምሮ ገልጿል፡፡

ወንጀል ፈጽሞ ከህግ ተጠያቂነት የሚያመልጥ እንደማይኖር ያስታወቀው ፖሊስ ንዴትን በመቆጣጠርና በትዕግስት የወንጀል ድርጊትን መከላከል እንደሚቻል አስታውቆ ከቅድመ መከላከሉ ባሻገር ወንጀል ሲፈፀም በፍጥነት ለፖሊስ ማሳወቅ እንደሚገባም አስታውቋል፡፡

2 comments

እዮብ መኮንን December 7, 2024 - 6:14 pm

መብራት ሄደ እዴ

Reply
በቃ አስኪ December 7, 2024 - 6:20 pm

ለዚህ ክፋቷ እሷንም እንደ ህፃንዋ መ*ደል ት*ት መስ*ል ማስተማሪያ ትሆናለች

Reply

Leave a Comment