መላው ዓለም ለአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመናት የነበረበት ባርነት በነጻነት ተተካ፣ ከውድቀት ተነሳ፣ መቃተቱ ተገታ ብንል እርሷን ተመክተን ነው፡፡ አባታችን ቅዱስ ኤፍሬም በረቡዕ ውዳሴ ማርያም “ነጸረ አብ እምሰማይ ወኢረከበ ዘከማኪ፣ ፈነወ ዋህዶ ወተሰብአ እምኔኪ” “አብ ከሰማያት ሆኖ ሲመለከት አንቺን የመሰለ አላገኘም አንድያ ልጁንም ወዳንቺ ልኮ ሰው ሆነ” ሲል ይገልጻታል፡፡ አንዳንዶች እምቤታችንን እርሱ እግዚአብሔር መረጣት የሚለውን ሲቀበሉ፣ እንድትመረጥ ሆና በንጽህና በቅድስና መገኘቷን መግለጽ አይሹምና ቅዱስ ኤፍሬም “አንቺን የመሰለ አላገኘም” ይላታል፡፡ በቅድስት ድንግል ማርያም መወለድ ወላጆቿ ቅዱስ ኢያቄምና ቅድስት ሀና ፍሬ አጊኝተዋል፡፡ ዓለም ደግሞ የመድኃኒቱን እናት፡፡
በመካንነት የነበሩት ወላጆቿ በንጽህና በቅድስና ቢኖሩም በወቅቱ የነበሩት ከካሕናተ ኦሪት ልጅ ስላልወለዱ መስዋዕታቸውን እንኳን ሊቀበሏቸው ፈቃደኛ አልነበሩም፡፡ ወላጆቿ ወደ እግዚአብሔር ጸልየው፣ ስዕለት ገብተው የወለዷት የልመናቸው መልስ ስትሆን፣ የሰው ልጅ ደግሞ ለአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመናት ያቀረበው የአድነን ልመና መልስ ናት፡፡ እመቤታችን ገና በቅድስት ሐና ማሕጸን ከነበረችበት ወቅት ጀምሮ ተአምራት ስታደርግ ነበር፡፡ ቤርሳቤህ ተባለች ሴት የሀናን መጽነስ ስትሰማ በደስታ ልትጎበኛት መጣች፡፡ ሁለቱንም አይኗን አጥታ የነበረችው ይህች ሴት ቅድስት ሐናን ወደ ቤቷ ገብታ እንኳን ደስ አለሽ ሆዷን ዳሰሰቻት፡፡ ድንገት በዚያው እጇ ዓይኗን ብትነካው ሁለቱንም አይኖቿ ቦግ በለው በሩላት፡፡ ይህን ምሳሌ አደርገው ድውያን እየመጡ ሆዷን ዳሰው ይፈወሱ ነበር፡፡
ሳሚናስ የሚባል የቅድስት ሐና የአጓቷ ልጅ ነበር፡፡ ይህ ሰው ታሞ ይሞታል፡፡ እመቤታችንን በሆዷ የያዘችው እናታችን ቅድስት ሐናም እጅግ ተወደው ነበርና በቤቱ ተገኝታ የአልጋውን ሸንኮር እየዞረች ስታለቅስ ከሞተበት ተነስቶ “የሰማይና የምድር ፈጣሪ አያት ሆይ ላንቺ ክብር ይገባሻል!!!” ብሎ መስክሮ አርፏል፡፡ አይሁድ የነገሩ አካሔድ አላማራቸውም፤ መጀመሪያ ድውያን የሀናን ሆድ እየዳሰሱ ተፈወሱ፣ ከዚያም የሞተው ዘመዷ ከሞት መነሳት ብቻ ሳይሆን ልዩ ክብር ያላት ጽንስ በማሕጸኗ እዳለ መሰከረ፡፡ እናም ቀድሞ የእነዚህ ዘር የነበሩ ዳዊትና ሰሎሞን አርባ፣ አርባ ዘመን ገዙን አሁን ከዚህች የሚወለድ ምን ሊያደርገን ነው? ሳይወለድ እንቅደመው ብለው በድንጋይ ሊወግራቻ ተነሱ፡፡
የራማው ልዑል ቅዱሰ ገብርኤል ይዟቸው ተሰውሮ ከከተማው ውጪ ሊባኖስ ተራራ ሲደርሱ ከመሸ ከጨለመ በኋላ ቅድስት ሐና ምጥ ያዛት በእዚያው በሊባኖስ ተራራም ቅድስት ድንግል ማርያም ተወለደች፡፡ ሰማያት ብርሃን ሰጡ፣ ቅዱሳን መላእክት አዲስ ምስጋና ተቀኙላቸው፣ የሊባኖስ ተራራም በብርሃን ደመቀ ተዋበ ምክንያቱም የብርሃን እናቱ ተወልዳለችና፡፡ በጨለማውስጥ የነበረው ዓለም ብርሃን የሚያይባት፣ የእውነተኛው ጸሐይ እናቱ ተወለደች፡፡ አባቷ ንጉስ ሰሎሞን “ሙሽራዬ ሆይ ከሊባኖስ ከእኔ ጋር ነዪ” እንዳለ በሊባኖስ ተራራ ተወለደች፡፡ ይህችን ብርሃን፣ የብርሃን እናት ገዳማውያን አባቶችና እናቶች በዚሁ ምስጋና ያመሰግኗታል፡፡ ገዳማቸውን እናግዝ፣ በዓታቸውን እናጽና፡፡
ድጋፍ ለማድረግ:-ሙትአንሳ ማር ቅዱሰ ሚካኤል አንድነት ገዳም
ኢትዮጲያ ንግድ ባንክ
1000442598391
ወይም
አቢሲኒያ ባንክ
141029444
የገዳሙ ስልክ ቁጥር:-0918077957 ወይም 0938644444