
ፈጥና በምትገባበት ወቅት ጥር 17 ዘግይታ በምትገባበበት ጊዜ ደግሞ የካቲት 24 ትጀምራለች፡፡ እንደ አቢይ ጾምም ሁሉ ሰኞ ቀን ነው የምትጀምረው፣ ጾመ ነነዌ፡፡ ከሰባቱ የሕግ አጽዋማት አንዷ ስትሆን ለመጀመሪያ ጊዜ የጾሟት የነነዌ ከተማ ሰዎች ናቸው፡፡ በትንቢተ ዮናስ የሰፈረው ታሪክ የነነዌ ሰዎች በፍጹም ጾምና ጸሎት ወደ እግዚአብሔር በመመለሳቸው መዳናቸውን ያሳያል፡፡ በዘፍጥረት 10÷11-12 እንደ ተጻፈው የነነዌ ከተማ በጤግሮስ ወንዝ ዳርቻ የምትገኝ ስትሆን መሥራቿም ናምሩድ ነው፡፡ ጥንታዊቷ የነነዌ ከተማ ለአሦራውያን መነሻ የሆነች፤ እጅግ ሰፊና ያማረች፤ የቅጥሯ ርዝመትም 12 ኪሎ ሜትር የሚሸፈን ነበር፡፡ በትንቢተ ዮናስ 4÷11 ደግሞ በከተማዋ ንጉሡ ሰናክሬም ብዙ ሕንጻዎችን ገንብቶ ነበር፡፡
የነነዌ ሕዝብ ኃጢአት በእግዚአብሔር ፊት እጅግ ቢበዛም በከንቱ ሊያጠፋቸው አልወደደምና ነቢዩ ቅዱስ ዮናስን እንዲያስተምራቸው ላከው፡፡ ዮናስ የስሙ ትርጓሜ ርግብ ማለት ሲሆን በዳግማዊ ኢዮአርብዓም ዘመነ መንግሥት የነበረ ነቢይ ነው፡፡ አባቱ አማቴ ሲባል እናቱ ደግሞ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ኤልያስን በቤቷ ያስተናገደችው የሰራጵታዋ መበለት ናት፡፡ ነቢዩ ቅዱስ ዮናስ መኖሪያው በገሊላ በጋትሔፈር ከተማ ድንበር ነው። ይህ ነቢይ ኢዮርብዓም ሶርያውያንን አባሮ የእስራኤልን ድንበር እንደሚመልስ ትንቢት የተናገረም ነው፡፡ አምላካችን እግዚአብሔር የነነዌን ሕዝብ እንዲያስተምረው ቢልከውም “አንተመሐሪ ነህ ነነዌ ልትጠፋ ነው ብዬ ተናግሬ ብትምራቸው ሐሰተኛ ነቢይ እባላለሁ” ብሎ ላለመታዘዝ እስራኤልን ለቆ በመርከብ ወደ ተርሴስ ሸሸ፡፡
እግዚአብሔርም ታላቅ ነፋስን አስነሥቶ መርከቧ በማዕበል እንድትመታ አደረገ፡፡ ከዮናስ ጋር በመርከቧ ተሳፍረው የነበሩ ነጋድያንም ያላቸውን ሀብት ወደ ባሕሩ መጣል ሲጀምሩ ነቢዩ ዮናስ ጥፋቱን ተገንዝቦ “ማዕበሉ በእኔ ምክንያት የመጣ ስለሆነ ንብረታችሁን ሳይሆን እኔን ወደ ባሕር ጣሉኝ” አላቸው፡፡ ወደ ባሕሩ ለመጣል ዕጣ በተጣጣሉ ጊዜም በዮናስ ላይ ስለወጣ ዮናስን ወደ ባሕሩ ጣሉት፡፡ ከእግዚአብሔር ዘንድ የታዘዘ ታላቅ ዓሣ ነባሪ ዮናስን ውጦት ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት አሳድሮ ወደ ነነዌ አደረሰው፡፡ እግዚአብሔር የቅል ተክል ጥላ አድርጎለት አረፈ፡፡ ተኝቶ ሲነሳም ተክሉን ትል በልቶት ደርቆ ስላየ አዘነ፡፡
እግዚአብሔርም “አንተ ላልደከምክበትና በአንድ ቀን በቅሎ ላደገ ቅል ስታዝን እነሆ በታላቂቱ ነነዌ ከተማ ያሉ ከአንድ መቶ ሃያ ሺሕ በላይ ሕዝብና እንስሳቱ እንደምን አያሳዝኑኝምን?” በማለት ነቢዩ ዮናስም ውሸታም ላለመባል መኮብለሉ ስሕተት መሆኑን አስረድቶታል፡፡ ዮናስም ነነዌ መሬት ላይ መድረሱን ባወቀ ጊዜ ከእግዚአብሔር መሸሽ አለመቻሉን ተረዳ፤ የነነዌ ሰዎችንም “ንስሐ ግቡ” እያለ መስበክ ጀመረ፡፡ የነነዌ ሰዎችም ንስሐ በገቡ ጊዜ እግዚአብሔር ይቅር ብሎ ከጥፋት አድኗቸዋል፡፡ ሐሰት እንዳይባልም እሳቱ እንደ ደመና ሆኖ ከላይ ታይቶአል፡፡ የታላላቁ ዛፍ ቅጠል እስኪጠወልግ ድረስ አድርቆ ለሕዝቡ አሳይቷቸዋል፡፡ ንስሐቸው በከንቱ እንዳልቀረ አስረድቷቸዋል፡፡ በእነዚህ የጾም ቀናት ገዳማውያንን እንደግፍ በዓታቸውን እናጽና፡፡
ድጋፍ ለማድረግ፦ሙትአንሳ ማር ቅዱሰ ሚካኤል አንድነት ገዳም
ኢትዮጲያ ንግድ ባንክ
1000442598391
ወይም
አቢሲኒያ ባንክ
141029444
የገዳሙ ስልክ ቁጥር:-0918077957 ወይም 0938644444