ቅድስት ቤተ-ክርስቲያን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደሙ ዋጅቶ የመሰረታት፣በክርስቶስ ክርስቲያን ለተባልን በሙሉ መሰብሰቢያችን የተቀደሰች ቤታችን ናት፡፡
ቤተ ክርስቲያን ስንልም ህንጻ ቤተ ክርስቲያን፣የክርስቲያን ወገን፣የምዕመናን አንድነት ወይም ማኀበረ ምዕመናን እንዲሁም እያንዳንዱ ምዕመን ማለታችን ነው፡፡
ገዳማት ደግሞ የቤ ክርስቲያናችን ስውር ጓዳዎችና የሚስጢር መዝገቦች፣የመማጸኛ ቅዱስ ስፍራዎች ናቸው፤የቤተ ክርስቲያናችን ሁለንተናዊ አገልግሎት መሰረት፣የተግባራዊ ክርስትና ምሳሌዎችም ናቸው፡፡የታላላቅ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት መፍለቂያዎችም ናቸው፣ገዳማት፡፡
እነዚህ ቤተ-ክርስቲያናትና እና ገዳማት መንፈሳዊ አገልግሎታቸውን እየሰጡ፣ትውልድንም በክርስቲያናዊ ስነ ምግባር እያነጹ ይቀጥሉ ዘንድ ገቢ ያስፈልጋቸዋል፡፡
ይህንን ገቢያቸውን ከሚያገኙባቸው መንገዶች ደግሞ በራሳቸው አቅም ገቢ የሚያመነጩ ስራዎችን ማከናወን እንዲሁም ምዕመኑ በሚሰጠው መባ እና አስራት በኩራ ይጠቀሳሉ፡፡
ይሁንና አንዳንዴ ተፈጥሮ ፊቷን ስታዞር፣ሰው ሰራሽም ተፈጥሯዊም ችግሮች ሲበረቱ ገዳማት የገቢ ምንጫቸውና ህልውናቸው ሙሉ በሙሉ ህዝበ ክርስቲያኑ በሚያደርገው ድጋፍ ላይ የተንጠለጠለ የሚሆንበት አጋጣሚም አለ፤ልክ ሙትአንሳ ማር ቅዱስ ሚካኤል አንድነት ገዳም በአሁኑ ወቅት እንደገጠመው አይነት ችግር ውስጥ ሲገኙ፡፡
በዚህ ገዳም የሚገኙ ገዳማዊያን ዛሬም ከጸሃይ፣ከብርድ፣ከዝናብ የሚከላከል መጠለያ አጥተው በከፍተኛ ችግር እየተፈተኑ የሚገኙ ነዉ፡፡ ገዳማዊያኑ ከነዚህ አስከፊ ችግሮች እንዲወጡ፣በወረዳ ቤተ-ክህነት፣በሀገረ ስብከትና በጠቅላይ ቤተ ክህነት ፕሮጀክት ጸድቆ በሊቃነ ጳጳሳት ቡራኬና የቅርብ ክትትል እየተደረገበት በመሰራት ላይ ሲሆን በእናንተ ደጋግ ለጋሾችና እንደየ መክሊታቸው ርብርብ በሚያደርጉ ምዕመናን ጥሩ ጅምርና ተስፋ ሰጭ የስራ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ይገኛሉ፡፡
ይሁንና ይህን ሰናይና የገዳማዊያኑን ችግር ለመቅረፍ የሚደረገውን ጥረት አንዳንድ ሰዎች ወደኋላ ለመጎተትና የገዳማዊያኑም ችግር እንዳይፈታ ችግር ለመፍጠር ሲሞክሩ እየተስተዋሉ ነው፡፡ ከነዚህም መካከል ቤተ ክርስቲያናችን መዋቅር እያላት ምንም አይነት መረጃ ሳይጠየቅ፣ ያለ ምንም መረጃ ምዕመኑ የሚያደርገው ድጋፍ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊፈጥሩ የሚችሉ ነገሮችን እያሰራጩ መሆኑን ታዝበናል፡፡ይህም በገዳሙ የሚኖሩ መነኮሳት ላይም ሆነ በገዳሙ እየተሰሩ ያሉ የልማት የስራ እንቅስቃሴዎች ላይ አሉታዊ ጫና ያሳርፋል፡፡
ገዳማዊያኑ ወደ ሚዲያ እንዲወጡ ያስገደዳቸው የከፋ ችግር ሆኖ ሳለ፣ ቢቻል ማገዝ ሲገባ ችግራቸው በደጋግ ሰጭ እጆች እንዳይፈታ ለማድረግ መረባረብ ገዳማዊያኑን ያሳዘነ ሆኗል፡፡
መታወቅ ያለበት እውነታ ግን ከቤተ ክርስቲያኗ የወጣ ምንም ብር አለመኖሩ ሲሆን፣ገዳሙ መረጃውን የሚፈልጉ አካላት በሙሉ በየትኛውም ሰዓት አግባብ በሆነ መልኩ መረጃን ማግኘት እንደሚችሉ ያረጋግጣል፡፡
ከዚህ ውጭ የገዳሙን ስም ያለ መረጃ ባልተገባ መልኩ እያነሱ የሚወነጅሉ አካላትን በህግ አግባብ የሚጠይቅ ይሆናል፡፡ ከሰሞኑ የገዳሙን ስም ያለ መረጃ ባልተገባ መልኩ ሲያነሱ የነበሩትን የህግ ሂደት፣ ገዳሙን በህግ እውቀታቸው በሚያገለግሉ የህግ ባለሙያዎች መረጃ እየተሰበሰበና እየተደራጀ ሲሆን በአጭር ጊዜ ውስጥም ጉዳዩ በህግ የሚያዝ ይሆናል፤ጉዳዩ የደረሰበትን ምላሽም ለህዝብ ጊዜውና ሰዓቱ ሲፈቅድ ይፋ ያደርጋል፡፡
ከዚህ ባሻገር ገዳሙ የካቲት 14/2017 ዓ.ም አጠቃላይ ስለ ገዳሙ ወቅታዊ ሁኔታ መረጃዎችን በተመለከተ ለመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚሰጥበት ከወዲሁ ያሳውቃል፡፡
#ሙትአንሳ ማር ቅዱስ ሚካኤል አንድነት ገዳም
የካቲት ፭/፪፻፲፯ ዓ.ም
2 comments
ከሙት አንሳ😂
የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ለመስጠት ችግር የለበትም ነገር ግን ሲኖዶሱ፣ የአዲስ አበባ አገር ስብከት ቤተክርስቲያኒቷ ለልማት ትግባብተው ቢሰሩ በየገጠሩ የተጎሳቊሉ ገዳማትና ቤተክርስቲያናት ልክ እንድ አዲስ አበባ ደብሮችና ካቴድራሎች መስራት በተቻለ ነበር