በሰሜን ወሎ ዞን አይነ ቡግና ወረዳ የሚገኙ አርሶ አደሮችን ድቅር በከፍተኛ ሁኔታ እያጠቃቸው ነው። በወረዳው በሚገኙ 14 ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ አርሶ አደሮች የዕለት ደራሽ ድጋፍ ካላገኙ የሚላስ የሚቀመስ የላቸውም።
አለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን መብት ወይም ግሎባል አልያንስ በደረሰባቸው አምስት ቀበሌዎች ብቻ ከ115 ሺ በላይ ሰዎች ይኖራሉ። የቀሪዎቹን ቀበሌዎች ቁጥር ከእነዚህ ቀበሌዎች ነዋሪዎች ቁጥር አንጻር መገመት የድርቁን ተጠቂ ቁጥር ከፍተኛነት ለመገመት ያስችላል ። ግሎባል አልያንስ ድጋፍ ባደረገላቸው ዘብሎ፣ ፈልፈሊቅ፣ ብርኳኳ፣ ደብረ እግዚ እና
ቆብ ቀበሌዎች ያገኘናቸው አርሶ አደሮች እንደነገሩን ድርቁ ከጸናባቸው ዓመታት ተቆጥረዋል።
የክረምት ዝናብ እጥረት ዝናብ ሲመጣም የበረዶ ሰብልን ማውደም፣የመሬት መንሸራተት፣የማዳበሪያ እጥረት፣የእርስ በእርስ ጦርነት፣የአየር ንብረት ለውጥ እና የእርስ በእርስ ጦርነት ለአመታት ከፍተኛ ዋጋ እያስከፈሏቸው ይገኛሉ። በአምራችነት ይታወቅ የነበረው አካባቢ የዕለት ድጋፍ ጥገኛ ከሆነ አመታት ተቆጥረዋል። አረጋውያን በመጦሪያቸው ወቅት የሰዎችን እጅ ይጠብቃሉ።ህጻናት በምግብ እጥረት ለመቀንጨር ተጋልጠዋል። አራሶች ለልጆቻቸው የሚያጡቡት ጡታቸው ደርቋል። ወጣቶች ተሯሩጠው በሌላ ስራ እራሳቸውን እንዳያስተዳድሩ በአካባቢው ያለው የእርስ በርስ ግጭት አልፈቀደላቸው። የዞኑ ነዋሪዎች ድጋፍ ፈላጊ ለመሆን ተገደዋል።
ኢትዮጵያውያን ባሉበት እና በቸገራቸው ወቅት ሁሉ ከጎናቸው የማይለው ግሎባል አልያንስ ከ3 ነጥብ 3 ሚልዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ የገዛቸውን 778 ኩንታል የበቆሎ ዱቄት በመያዝ ለወገን አለኝታ መሆኑን አስመስክሯል። በዚህ ወቅት ወደ አካባቢው መጓዝ እና ለወገን መድረስ ፈታኝ በሆነበት በዚህ ወቅት በአርቲስት እና አክቲቪስት ታማኝ በየነ የሚመራው ግሎባል አልያንስ በኢትዮጵያ ተወካዩ በፍቃዱ አባይ አማካኝነት አይነ ቡግና ወረዳ ቆብ ቀበሌ በመገኘት ድጋፉን አድርሷል። በቆብ ቀበሌ በመገኘት ከግሎባል አልያንስ የተላከውን እና ከ3.3 ሚሊዮን ብር የሚያወጣውን 778 ኩንታል የበቆሎ ዱቄት የተረከቡት የሀገር ሽማግሌዎች ፣የኃማኖት አባቶች፣የሴቶች ተወካዮ፣የቀበሌው አስተዳዳሪ፣የእርዳታ አስተባባሪ ተወካዮች እና አርሶ አደሮችም ግሎባል አልያንስ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ስላደረግላቸው ድጋፍ ከልብ አመስግነዋል። የበልግ ወቅት ዝናብን መምጣት ተስፋ እያደረጉ ባሉበት እና ህብረተሰቡ በከፍተኛ ደረጃ በድርቅ እየተጠቃ ባለበት አስቸጋሪ ወቅት አብሮአቸው ስለሆነ ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል። በአካባቢው ያለው ጸጥታ ስጋት እና አስቸጋሪ የመልከአ ምድርን አቀማመጥና የአየር ንብረት ችግር ተቋቁሞ ለወገን መድረስ ዋጋው የላቀ መሆኑን ገልጸዋል።
ሌሎች ድጋፍ አድራጊዎችም በወረዳው ያለውን የከፋ ድርቅ በማየት እንደ ግሎባል አልያንስ ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አስተላልፈዋል።




