#FastMereja | ኢትዮ ተሸከርካሪዎች አስመጪ ባለቤቶች ማህበር የጥራት ደረጃ ሰርተፍኬት ምክንያት ሥራ መስራት መቸገራቸውን ለንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚንስቴር በደብዳቤ አሳውቀዋል።
ኢትዮ ተሸከርካሪዎች አስመጪ ባለቤቶች ማህበር ባደረገው ወቅታዊ ስብሰባ ላይ እንደተነሳው መንግስት እንደ አዲስ ባስቀመጠው የኤሌክትሪክ መኪኖች የጥራት ደረጃ ሰርተፍኬት ምክንያት በአግባቡ መሥራት አልቻልንም። እንደከዚህ ቀደሙ የማህበራችን አባሎች ስራቸውን በቀልጣፋነት ለማከናወን ከመቸገርም በላይ እንደሀገር ጉምሩክ ከመኪና አስመጪዎች የሚጠብቀውን ቀረጥና ታክስ ለማሳካት እና ለመክፈል አዳጋች ሆኖብናል ብለዋል፡፡
በተጨማሪም አባሎቻችን በአንድ ተሽከርካሪ እስከ 200 ዶላር ወጪ እያወጡ ሲሆን በተለይም አገር ውስጥ ለገቡትም እንዲሁም በቅርቡ ለሚያስገቡትም መኪኖች ይህን ክፍያ ለመክፈል የተገደዱ ሲሆን በተለይም ይህንን ሰርተፍኬት ለማሰራት ከሚፈጀው ወራት አንጻር አለአግባብ ለሆነ ከፍተኛ የዲሜሬጅ ወጪ መጋለጣቸውን አንስተዋል፡፡
እነዚህም ወጪዎች በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የውጭ ምንዛሪ መሆናቸው እንደ ሀገር የሚፈጥረውንም ጫና ከግምት ውስጥ ማስገባት እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።
ኢትዮ ተሸከርካሪዎች አስመጪ ባለቤቶች ማህበር ይህ አካሄድ አገርን እንደሚጎዳ እና ቀረጥና ታክስ መሰብሰብ ላይ ትልቅ ችግር ከመፍጠሩም ባሻገር አስመጪዎች ከሰርተፍኬቱ ጋር በተያያዘ የሚያወጡት ወጪ በገቢዎች እንደወጪ ታስቦ አለመያዙ ሌላኛው ማነቆ ሆኖብናል ሲሉ አስታውቀዋል፡፡
አያይዘውም ይህ ሁሉ ዶላር ለጎረቤት አገር መከፈሉ አግባብነት እንደሌለው ተገንዝቦ ሚንስቴር መስሪያ ቤቱ አስፈላጊውን መፍትሄ እንዲያደርግልን እንዲሁም ችግራችንን እንዲፈታልን ዘንድ በአክብሮት እንጠይቃለን ሲሉ (ግልባጭ * ለገንዘብ ሚንስቴር * ለጉምሩክ ኮሚሽን) በማድረግ አስታውቀዋል፡፡
ኢትዮ ተሸከርካሪዎች አስመጪ ባለቤቶች ማህበር በአቤቱታው እንዳስታወቀው የማህበራችን አባሎች አብዛኛዎቹ ሀገራዊ ግዴታቸውን በመወጣት በከፍተኛ ደረጃ ግብር ከፋይ በተደጋጋሚ ተሸላሚ መሆናቸው አውስቷል፡፡
