banner

“እንዳለሁ አበራለሁ” የተሰኘና ኦቲዝም ላይ ትኩረቱን ያደረገ መፅሀፍ በአሜሪካን ሃገር ተመረቀ።

#FastMereja I በደራሲ ማክዳ አርሺ Shining As I am በእንግሊዝኛ ግጥም ተፅፎ በታገል ሰይፉ ወደ አማረኛ የተተረጎመው “እንዳለሁ አበራለሁ” የተሰኘው መፅሃፍ የካቲት 16 ቀን 2017 ዓ.ም በአሜሪካን ሃገር ሲልቨር ስኘሪንግ ሜሪላንድ ቬተራንስ ፕላዛ በርካታ ኢትዮጵያውያን በተገኙበት ተመርቋል::

“እንዳለሁ አበራለሁ” ለልጆች ኦቲዝም ምን እንደሆነ በቀላል ቋንቋ የሚያስረዳ ሲሆን ታሪኩ አንድ የኦቲዝም ተጠቂ የሆነ ልጅ ቀኑን ሙሉ የሚገጥመውን ነገር የሚገልፅበት እና በልዩነት ውስጥ ያለን ውበት አጉልቶ የሚያሳይ ስለመሆኑ ታውቋል፡፡ ለልጆችም ትዕግስትን፣ ሌሎችን መቀበልን እና ርህራሄን ያስተምራል ተብሏል፡፡

በምርቃቱ ላይ የመፅሃፉ ደራሲ ማክዳ አርሺ ኦቲስቲክ ልጆች አለምን የሚገነዘቡበት መንገድ ልዩ ነው ያሉ ሲሆን ሆኖም በሃገራችን እንደሚታሰበው ኦቲዝም “እብደት” ወይም “እርግማን” ሳይሆን በተፈጥሮ የሚከሰት ሰዎች ከማያስተውሉት አነስተኛ የባህሪ ልዩነት አንስቶ እጅግ በጣም ከፍተኛ እገዛና እርዳታ የሚያስፈልገው የአዕምሮ እድገት ልዩነት መሆኑን ተገንዝቦ ልጆቹ የፈጣሪ ስጦታ መሆናቸውን አምኖ መቀበል ያስፈልጋል፤ እስከዛሬ ግን ይህን በቅጡ አልተረዳነውም ሲሉም አክለዋል።

ብዙ ወላጆች ከማህበረሰብ የሚደርስባቸው መገለልና እነሱም ስለ ህመሙ በቂ መረጃ ስለማይኖራቸው ለከፍተኛ ስቃይና እንግልት እንደሚዳረጉም አንስተዋል።

ኑሯቸውን በሃገረ አሜሪካ ያደረጉት ማክዳ አርሺ ከዚህ ቀደም “የአለም መብራቶች” የተሰኘ የልጆች መፅሃፍ ደራሲ ሲሆኑ በዚሁ መፅሃፍ moms choice award የተሰኘ አሜሪካን ሃገር የሚገኝ ሽልማትን ጨምሮ የአምስት ሽልማቶች አሸናፊ መሆናቸው ይታወሳል::

“እንዳለሁ አበራለሁ” በአሁኑ ወቅት Amazon ላይ እየተሸጠ ሲሆን Shining As I am “Amazon Best seller” መሆኑም የሚታወቅ ነው:: በቅርብ ጊዜ በሃገር ውስጥ ለሚገኙ አንባቢያን ይደርሳልም ተብሏል::

#ልዩ_ልዩ




Leave a Comment