#FastMereja I ትኩረት ለሴቶች እና ለህፃናት ማኀበር በ850 ብር ማህበሩን እንደግፍ የሚል ጥሪ አቅርበዋል። ማህበሩ ዛሬ መጋቢት 22/2017 ዓም በማእከሉ ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ በ850 የቀረበውን ቲሸርት በመግዛት ማህበሩ የሚያሰራውን የተሰጡ ልቦች የተሰኘውን G+6 ህንፃ እንገባ ተብሏል።
ህንፃውን ገንብቶ ለማጠናቀቅ 60 ሚሊዮን ብር የሚጠይቅ ሲሆን ህንፃው በውስጡ ልዩ ፍላጎት ላላቸው ህፃናት መዋያ፣ የምገባ ማዕከል እና የእናቶች መሰባሰቢያ እንደሚሆን ነው የተገለፀው።
በመሆኑም ማህበሩ በየአመቱ እንደሚያደርገው እስከ 2200 ተሳታዎች የሚገኙበት ገቢ ማሰባስበ እና ግንዛቤ ማስጨበጫ ከሰፖርታዊ እንቅስቃሴ ጋር መጋቢት 28/2017 ዓ.ም ከጠዋቱ 2:30 አስከ 6:00 ሰዓት የሚቀይ ዝግጅት በአድዋ ድል መታሰቢያ ለማድረግ ዝግጅቱን አጠናቋል፡፡
ቲሸርቶቹን በመግዛት በአድዋ ሙዚየም የሚካሄደውን ፕሮግራም ታዳሚ መሆን የሚቻል ሲሆን ቲሸርቶቹን በማዕከሉ እና በኤግዚብሽን ማዕከል ኤክስፖ ላይ ማግኘት ይቻላል ተብሏል።
ሙሉ በሙሉ ልዩ ፍላጎት ያላቸው ህጻናት ላይ ያደረገው ማዕከሉ በከፊል ንፋስ ስልክ ላፍቶ እና ሸገር ከተማ ፉሪ ክፍለ ከተማ ሙዳ ፉሪ ወረዳ ላይ የሚገኙ 164 ልዩ ፍላጎት ያላቸው ህፃናት እና 164 እናቶችን በአጠቃላይ 344 ሰዎችን እየደገፈ እንደሚገኝ ተገልጿል።
ትኩረት ለሴቶችና ለህፃናት ማህበር ላለፉት 18 አመታት በአዲስ አበባ፣ በኦሮሚያ እና በደቡብ ኢትዮጵያ ወላጆቻቸውን ላጡና ለችግር የተጋለጡ ህፃናት እና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ሴቶች ድጋፍና እንክብካቤ እንዲሁም የኤችአይቪ ኤድስን ስርጭትን ለመቀነስ የተለያዩ ፕሮግራሞችን ነድፎ በአጠቃላይ 12,000 ሺህ የሚደርሱ የህብረተሰብ አካላትን ሲደግፍ ቆይቷል።




