#FastMereja I በሮማንያ ለሚካሄደው የኢትዮጵያ የባህልና ቢዝነስ ፌስቲቫል የመክፈቻ ስነ ስርዓት በኢንተር ሌግዠሪ ሆቴል በደመቀ መልኩ ተከናውኗል።
በመክፈቻ ፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር እንደገና አበበ ኢትዮጵያ ከሮማንያ ጋር ላለፉት ስድስት አስርት አመታት በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ በፖለቲካዊ ትብብር፣ በንግድና በዲፕሎማሲ መስኮች ሲሰሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል።
ሚኒስትር ዲኤታው ኖርዲክ ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማ ያዘጋጀው ይህ ዝግጅት ከላይ ከተጠቀሱት ዘርፎች በተጨማሪ የባህል ዲፕሎማሲን፣ በቱሪዝሙ ዘርፍ አዲስ የገበያ መዳረሻን ለመፍጠርና አለማቀፍ ትብብርን ለማጎልበት ይረዳል ሲሉ ጠቅሰዋል።
የሮማንያ ፓርላማ ምክትል አፈ ጉባኤ የተከበሩ አቶ ካሊን ፍሎሪን ግሮዛ ሮማንያ ከአፍሪካ አህጉር ጋር የምትከተለውን “የሮማንያ -አፍሪካ የጋራ የሰላም፣ የእድገትና የትምህርት ትብብር” ስትራቴጂ ስኬታማ ለማድረግ ኢትዮጵያ የማዕከላዊነት ሚናዋን የምትጫወት በመሆኑ ፌስቲቫሉ አይነተኛ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።
ክቡር ምክትል አፈ ጉባኤው አያይዘውም ፌስቲቫሉ በአይነቱ የመጀመሪያ ከመሆኑም ባሻገር በሁለቱ ሃገራት መካከል ያለውን በክብርና በግልፅነት ላይ የተመሰረተ ግንኙነትን አንድ ደረጃ ከፍ የሚያደርግ እንደሆነ እምነታቸውን ገልፀዋል።
በቀጣይም በሰላም፣በፀጥታና ዘላቂ ልማትን በማረጋገጥ ረገድ በጋራ ለመስራትና አስፈላጊውን ድጋፍ ለሚደረግ ዝግጁ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
በሮማንያ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ አንድነት በቀለ በበኩላቸው በሮማንያ የኢትዮጵያውያን ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ተከትሎ ኮሙዪኒቲ መቋቋሙን ገልፀው ይህ ፌስቲቫል ሃገራችን ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ የባህል፣ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ለማስተዋወቅ እና የቢዝነስ እድሎችንና ትስስሮችን ከሮማንያ ጋር ለመፍጠር ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል ሲሉ አስረድተዋል።
ኖርዲክ ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማ ለረጅም አመታት በተለያዩ የሁነት ዝግጅቶች ላይ በሃገር ውስጥም በውጭም ሲሳተፍ እንደነበር የገለፁት የኖርዲክ ትሬዲንግ ስራ አስኪያጅ አቶ ወንድሜነህ አምባዬ ዝግጅቱ ለሃገራችን በባህልና በቢዝነስ ዘርፉ መልካም እድሎችን ይዞ እንደሚመጣ በማመን የተዘጋጀ እንደሆነ አብራርተዋል። በዕለቱ ጥሪ የተደረገላቸው በርካታ የክብር እንግዶች ተገኝተዋል።




