#FastMereja I የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የ70ኛ እና የማስተማሪያ ሆስፒታለችን 100ኛ ዓመት ክብረ በዓልን ምክንያት በማድረግ የፍራፍሬ ተክሎች ችግኝ ተከላ መርሀ-ግብር በዩኒቨርሲቲው አጼ ቴዎድሮስ ግቢ በሚገኘው የመካነ-ዕጽዋት ቁጥር – 2 ግቢ ተካሂዷል፡፡
በዩኒቨርሲቲው ግብርናና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ አስተባባሪነት በተካሄደው በዚህ የፍራፍሬ ተክሎች ችግኝ ተከላ ዘመቻ፣ የዩኒቨርሲቲውን ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስራት አጸደወይንን ጨምሮ ሌሎች የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮችና መምህራን ተሳትፈዋል፡፡
በተመጣጠነ ምግብ ይዘታቸው ከፍተኛ የሆኑ ፍራፍሬዎችን መትከል፣ ደኖችን መልሶ ከማቋቋም ባሻገር ለጤናማ የምግብ ስርዓት አይነተኛ ሚና እንደሚኖራቸው የገለጹት የዘመቻው አስተባባሪ ዶ/ር አለምነው ታገለ ናቸው፡፡ የማንጎ፣ የአቮካዶ፣ የዘይቱንና የቡና ተክሎችን በዕለቱ ዘመቻ መትከል እንደተቻለ አስተባባሪው አክለው የገለጹ ሲሆን፣ ለጎንደር ከተማ ማህበረሰብና ለተለያዩ ተቋማት 17,100 የአትክልትና የፍራፍሬ ችግኞች በነጻ ለማሰራጨት እንደተዘጋጁ የዶ/ር አለምነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በዘመቻው የተሳተፉት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስራት በበኩላቸው፣ ዩኒቨርሲቲው በየዓመቱ “አረንጓዴ አሻራ” የማስቀመጥ መርሀ-ግብር እንደሚያከናውን ገልጸዋል፡፡ የአትክልትና የፍራፍሬ ችግኞች ላይ ልዩ ትኩረት ያደረገው ይህ ዘመቻ ግን ከባለፉት ዓመታት የተለየ እንደሚያደርገው አክለው የተናገሩ ሲሆን፣ ክትትልና ተገቢውን እንክብካቤ መሰረት ያደረገ መሰል ዘመቻ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ፕሬዚዳንቱ አፅንኦት ሰጥተው አሳስበዋል፡፡




