#FastMereja I ዓለም ፍሬ ፒንክ ሃውስ ካንሰር ፋውንዴሽን የበጎ አድራጎት ድርጅት ዓመታዊ የጡት ካንሰር ወርን ምክንያት በማድረግ “ብርታትሽ ብርታቴ” በሚል መሪ ሐሳብ በዛሬዉ እለት ህዳር 7 ቀን 2018 ዓ.ም የእግር ጉዞ እና ማስ ስፖርት በማስተር ሄኖክ መሪነት አካሂዷል።
በዛሬዉ የጡት ካንሰር የግንዛቤ ማስጨበጫ ወር ማጠቃለያ ላይ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት እና ባለሙያዎች እንዲሁም ከሶስት ሺህ በላይ ተሳታፊዎች በተገኙበት የማስ ስፖርት እና የእግር ጉዞ የተካሄደዉ።
የአለም ፍሬ ፒንክ ሀዉስ ፋዉንዴሽን መስራች የሆኑት ደ/ር ፍሬህይወት ደርሶ በጡት ካንሰር የምንወዳቸውን እንዳናጣና እኛም እንዳንጎድል የጡት ካንሰርን መከላከል እንዲሁም በጊዜ ተመርምሮ ታክሞ መዳን እንደሚቻል በዛሬዉ መርሀ-ግብር ላይ ገልፀዋል።
በዛሬዉ መርሀ-ግብር ላይ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ኢርጎጌ ተስፋዬን ጨምሮ የጤና ሚኒስቴር ሀላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
ዶ/ር ኢርጎጌ ተስፋዬም ቅድመ ምርመራና ህክምናን በማስፋት ማህበረሰቡን ማስገንዘብና ተባብሮ ለመስራት ጥሪ አቅርበዉ ተቋማቸው ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን በመግለፅ ለአለም ፍሬ ፒንክ ሀውስ ፋውንዴሽን የ2ዐዐ ሺህ ብር ድጋፍ አድርገዋል።
እንዲሁም አዋሽ የገንዘብ ቁጠባና ህብረት ስራ ማህበር ለፒንክ ሀዉስ ፋዉንዴሽን የመቶ ሺህ ብር ድጋፍ አድርጓል። በተጨማሪም በርካታ መንግስታዊ እንዲሁም የግል ድርጅቶች ለፒንክ ሀዉስ ፋዉንዴሽን የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ አብረዉ እንደሚሰሩም መልእክት አስተላልፈዋል።
ማስተር ሄኖክ ” ንቁ: ብርቱ: ጀግና ትውልድ” ለመፍጠር እየሰራ የሚገኝ በኢትዮጽያ የመጀመሪያዉ ሺዎችን ከቦርጭ፣ ከኮሌስትሮል፣ ከውፍረት ስኳር እንዲሁም ደም ግፌት ያላቀቀ የጀግና ትውልድ ኘሮጀክት በአካል ብቃት እና በህይወት ክህሎት ስልጠና እየሰጠ የሚገኝ ወጣት ሲሆን በዛሬዉ የማስ ስፖርት ላይም በመገኘት የማስ ስፖርቱን መርቷል።




