banner

የአፍሪካ ሀገራት ከሀገራዊ በጀታቸዉ 1% ለባህል ዘርፉ እንዲመድቡ ተጠቆመ!

#FastMereja : ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናት ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር በዛሬዉ እለት የባህልና ኪነ ጥበብ ዘርፍን ለማበረታታት ዩኒቨርሲቲዎችና የመንግስት ተቋማት ሊኖራቸዉ ስለሚገባ ሚና የግማሽ ቀን አዉደ ጥናት ተካሂዷል።

በዛሬዉ መርሀ-ግብር ሰላም ኢትዮጵያ እያከናወናቸዉ ከሚገኙ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ ኮኔክት ፎር ካልቸር አፍሪካ( Connect For Culture Africa) ፕሮግራም ሲሆን ይህም የአፍሪካ ሀገራት ከአጠቃላይ ሀገራዊ በጀታቸው 1% ለባህል እና ኪነ-ጥበብ ዘርፉ እንዲመድቡ አቅጣጫ ለማሳየት እና ከዘርፉ ባለሙያዎች ጋር ለመወያየት የተዘጋጀ አዉደ ጥናት ነዉ።

በአውደ ጥናቱ ላይ ምሁራን፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ ተመራማሪዎች፣ የባህል ተቋማት እና የሚዲያ ባለሙያዎች የተሳተፉ ሲሆን በማስረጃ እና በጥናት የተደገፉ መረጃዎችን ለኢትዮጵያ መንግስት በማቅረብ አብሮ ለመስራት የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል።

በዛሬዉ ዝግጅት ላይ የዩንቨርሲቲ እና የመንግስት ተቋማትን ሚና ጨምሮ ለባህልና ለፈጠራ ኢንዱስትሪዎች እስካሁን ድረስ እየተመደበ ያለውን በጀት ላይ በተደረገ ጥናቶች የተገኙ ግኝቶችም ቀርበዋል።

የባህልና ኪነጥበብ ዘርፍን ለማበረታታት ዩኒቨርስቲዎች መረጃዎችና አቅጣጫዎችን በመስጠት መደገፍ እንዳለባቸው እና በአውደ ጥናቱ ላይ የቀረቡት መረጃዎችና አቅጣጫዎች ለመንግስት ጥቆማ ለመስጠት እና መንግስት ድጋፍ እንዲያረግ ታልሞ የተዘጋጀ እንደሆነ የሰላም ኢትዮጵያ የፕሮግራም ዳይሬክተር አቶ ሲሳይ መንግስቴ ገልፀዋል።

ሰላም ኢትዮጵያ ትኩረቱን በባህልና እና ኪነ ጥበብ ዘርፍ በማድረግ የሚንቀሳቀስ አለም አቀፍ ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት ሲሆን በሀገራችን በ1997 ዓ.ም በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን የምዝገባ ቁጥር 1204 ተመዝግቦና ህጋዊ እውቅና አግኝቶ በኢትዮጵያ የባህል ዘርፍ ለኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ልማት የሚያደርገውን አስተዋፅኦ በመለየት ከሙያ ማህበራት ፣የልማት ድርጅቶች እና የመንግስት ተቋማት ጋር ጠንካራ የስራ ትስስር በመፍጠር እና በጋራ በመስራት አመርቂ ውጤቶችን ሲያስመዘግብ ቆይቷዋል፡፡





Leave a Comment