#FastMereja I አዲስ አበባ የንግድ ልውውጥን ከታሪካዊ እና መንፈሳዊ እሴቶች ጋር የሚያስተሳስር ታላቅ ዓለም አቀፍ ኤክስፖ ልታስተናግድ መሆኑ ተገለጠ። ከየካቲት 9 እስከ የካቲት 13 ቀን 2018 ዓ.ም (February 16-20/2026) በአዲስ አበባ አንድነት ፓርክ የሚካሄደው “ኢትዮ አረብ ረመዳን ኤክስፖ 2026″፣ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የንግድ መድረክ ያላትን ሚና የሚያጎላ ታሪካዊ ክስተት እንደሚሆን ተመልክቷል።
ለአምስት ተከታታይ ቀናት በሚቆየው በዚህ ግዙፍ የንግድና የኢንቨስትመንት መድረክ ላይ ከ10 በላይ አገራት የተውጣጡ 400 የሚጠጉ ታዋቂ ነጋዴዎችና የቢዝነስ መሪዎች ይሳተፋሉ። ዝግጅቱ የውጭ ምንዛሪ ፍሰትን በማሳደግ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ አዲስ መነቃቃትን ከመፍጠሩ ባለፈ፣ የሀገር ውስጥ አምራቾችና ሥራ ፈጣሪዎች ምርቶቻቸውን ለዓለም ገበያ የሚያስተዋውቁበትና ከዓለም አቀፍ አቻዎቻቸው ጋር የረጅም ጊዜ የንግድ ትስስር የሚፈጥሩበት ወርቃማ አጋጣሚ እንደሚፈጥር ተገልጿል።
”አርዱል ሰላም” እና የዓለም አቀፍ እንግዶች መገኘት
ይህንን ዝግጅት ልዩ የሚያደርገው በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚሊዮኖች የሚወደዱ ታዋቂ (VVIP) ግለሰቦች ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ምድር ተገኝተው የዝግጅቱ አካል መሆናቸው ነው። እነዚህ ታዋቂ ሰዎች በቆይታቸው ትምህርታዊና መንፈሳዊ ግንዛቤዎችን ለታዳሚው የሚያካፍሉ ሲሆን፣ ይህም ለባህላዊ ውይይትና ለሕዝቦች መግባባት ከፍተኛ ፋይዳ እንደሚኖረው ታውቋል።
”ኢትዮጵያ (ሀበሻ) የሰላምና የፍትሕ ምድር” በሚል መሪ ቃል፣ ዝግጅቱ ኢትዮጵያ በእስልምና ታሪክ ውስጥ ያላትን የማይተካ ቦታ ዳግም ለዓለም ያስተዋውቃል። ነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ተከታዮቻቸውን “ወደዚች የሰላም ሀገር ሂዱ፤ ፍትሐዊ መሪ ከበዳዮች ይጠብቃችኋል” በማለት የመሰከሩላትን የሀበሻ ምድር ክብር የሚያዘክሩ ልዩ የመድረክ መርሐግብሮች በረመዳን ዋዜማ እንደሚቀርቡም ተጠቁሟል።
የዝግጅቱ አስተባባሪዎች ይህንን ታሪካዊ መሠናዶ ስኬታማ ለማድረግ የማኅበረሰብ መሪዎች፣ ጋዜጠኞችና ባለሙያዎች የኢትዮጵያን እንግዳ ተቀባይነትና ውበት ለዓለም ለማሳየት በጋራ እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበዋል።
ባጠቃላይ ይህ ኤክስፖ የኢትዮጵያን የንግድ አቅም ከመገንባት ባለፈ፣ ሀገሪቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን የታሪክና የሰላም ተምሳሌትነት ዳግም የሚያድስ ብርቅዬ መድረክ እንደሚሆን ይጠበቃል።




