banner

በ”ተስፋ አዲስ” ማዕከል ለሚገኙ የካንሰር ህሙማን ህፃናት የገና በዓል በደመቀ ሁኔታ ተከበረ

#FastMereja I በ”ተስፋ አዲስ” ማዕከል የህክምና እርዳታ ለሚያገኙ የካንሰር ህሙማን ህፃናትና ወላጆቻቸው፣ በወጣት ሜላት ንጉሴ አስተባባሪነት የገና በዓል በልዩ ሁኔታ ተከብሮ ዋለ።

በበጎ ፈቃደኝነት በተሰባሰቡ ወዳጆችና ጓደኞች ድጋፍ በተዘጋጀው በዚህ መርሐ-ግብር፣ በመካከሉ ለሚገኙ 54 ህፃናት አዳዲስ አልባሳት እና ጫማዎች የተበረከቱ ሲሆን፣ ይህም ህፃናቱ በዓሉን በሙሉ ተስፋና ደስታ እንዲያሳልፉ አድርጓቸዋል።

የበዓሉ አስተባባሪ ሜላት ንጉሴ እንደገለጸችው፣ ለህፃናቱና ለወላጆቻቸውም ጨምሮ ከ100 በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የምሳ ግብዣ ተደርጓል። “ምንም ነገር ሳይጎድል በዓሉን በደስታ አክብረናል” ስትል የገለጸችው ሜላት፣ ለዚህ ስኬት ከጎኗ የቆሙ ጓደኞቿንና ወዳጆቿን አመስግናለች።

አስተባባሪዋ አክላም፣ ቤታቸውንና የግል ጉዳያቸውን ትተው በማዕከሉ በመገኘት ከህፃናቱ ጋር የዋሉትን በጎ ፈቃደኞች በማድነቅ፣ ከወላጆች የተገኘው ምርቃትና ደስታ ለሁላችንም ትልቅ ስጦታ ነው ብላለች።

የ”ተስፋ አዲስ” ማዕከል በካንሰር በሽታ ለተጠቁ ህፃናትና ከየክፍለ ሀገሩ ለሚመጡ ወላጆቻቸው ጊዜያዊ ማረፊያና ድጋፍ በመስጠት የሚታወቅ ሲሆን፣ እንዲህ ያሉ በጎ ተግባራት ለህሙማኑ ስነ-ልቦናዊ ጥንካሬ ትልቅ ሚና እንደሚጫወቱ ይታመናል።





1 comment

'ነገን ላይ እጓጓለሁ' January 7, 2026 - 6:39 pm

ሜሉ ረጅም ዕድሜ 🙏🙏🙏

Reply

Leave a Comment