banner

ረዳት ሜዲካል ፕላዛ የገናን በዓል ምክንያት በማድረግ ለካንሰር ህሙማን የነፃ ህክምና ስጦታ አበረከተ።

#FastMereja I ረዳት ሜዲካል ፕላዛ የዘንድሮውን የገና በዓል ምክንያት በማድረግ በስሩ የሚገኘውን አዲሱን “የክብር ደስታ የካንሰር ማዕከል” ስራ ማስጀመሩንና ለህሙማን የነፃ ህክምና ስጦታ ማዘጋጀቱን አስታወቀ።

​ተቋሙ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተጠቀሰው፣ በበዓል ስጦታነት ለ5 የጡት ካንሰር ህሙማን ሙሉ የኬሞቴራፒ ሕክምና በነፃ የሚሰጥ ሲሆን፣ በሌሎች የኦንኮሎጂ አገልግሎቶች ላይ ደግሞ ከ20 እስከ 30 በመቶ የሚደርስ የዋጋ ቅናሽ ተደርጓል።

ይህንን የነፃ ህክምና እድል መጠቀም የሚፈልጉ ህሙማን በ9477 የአጭር ስልክ መስመር ላይ በመደወል መመዝገብ እንደሚችሉ ተገልጿል።

​በመግለጫው ላይ በካንሰር ዘርፍ ላይ በስፋት የሚሰሩት “አለምፍሬ ፒንክ ሀውስ” እና “ንጋት የጡት ካንሰር ድጋፍ ቡድን” ተገኝተው ስለ ጡት ካንሰር ግንዛቤና ወቅታዊ ሁኔታ መልዕክት አስተላልፈዋል። ድርጅቶቹ እንደገለጹት፤ የካንሰር ህክምና የሚጠይቀው ወጪ ከፍተኛ መሆንና የዜጎችን ኪስ መፈተኑ ለህሙማን ስቃይ መጨመር ምክንያት በመሆኑ፣ እንደ ረዳት ሜዲካል ፕላዛ ያሉ ተቋማት የሚያደርጉት ድጋፍ የሚበረታታ ነው ብለዋል።

የክብር ደስታ የካንሰር ማዕከል​ መቋቋም ዋነኛ ዓላማ የካንሰር ህክምናን ቴክኖሎጂ ቀመስ በማድረግ ተደራሽነቱን ማሻሻልና በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚደርሰውን ጫና መቀነስ እንደሆነ ተገልጿል። ረዳት ሜዲካል ፕላዛ ከዚህ ቀደም በኒውክሌር ህክምና እና በዘመናዊ የህክምና መሣሪያዎች ዘርፉን ሲያዘምን የቆየ ሲሆን፣ በተለይም የህክምና ባለሙያዎች እውቀታቸውን ብቻ ይዘው በፕላዛው በሚገኙ መሣሪያዎች አገልግሎት የሚሰጡበትን አሰራር በመዘርጋት ይታወቃል።

​ይህ ልዩ የበዓል ተነሳሽነት እጅ አጥሯቸው ለሚገኙ ወገኖች እፎይታን ለመስጠትና ስለ ቅድመ ካንሰር ምርመራ ያለውን የግንዛቤ ክፍተት ለመሙላት የታለመ መሆኑም በመግለጫው ወቅት ተመላክቷል።





Leave a Comment