#FastMereja I በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አስራት አጸደወይንን በኤምባሲያቸው ተቀብለው ባነጋገሩበት ወቅት ለዩኒቨርሲቲው የመጻሕፍት ስጦታ አበርክተዋል።
አምባሳደሩ ያበረከቱት ስጦታ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሃሪ ትሩማንን ታሪክና ስራዎች የሚዘክሩ መጻሕፍት ሲሆኑ፣ ይህም በሁለቱ አካላት መካከል ያለውን የቆየ አጋርነት የሚያጠናክር መሆኑ ተገልጿል። ስጦታው በተለይም እ.ኤ.አ በ1950ዎቹ በፕሬዝዳንት ትሩማን ዘመን የተጀመረውን ታሪካዊ ግንኙነት እውቅና ለመስጠት የታለመ ነው።
ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በቅርቡ ቤተ-መጽሐፍቱን በፕሬዝዳንት ሃሪ ትሩማን ስም ለመሰየም ለወሰነው ውሳኔ አምባሳደር ማሲንጋ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ይህ እርምጃ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የትምህርትና የባህል ትብብር ይበልጥ እንደሚያጎላው ተመልክቷል።
በተጨማሪም አምባሳደሩ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የተመሰረተበትን 70ኛ ዓመት እንዲሁም ለዘመናዊ ሕክምና መሰረት የሆነው የማስተማሪያ ሆስፒታሉ የተቋቋመበትን 100ኛ ዓመት በዓል በማስመልከት የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከአሜሪካ መንግሥት ጋር ባለው የረጅም ዘመን ግንኙነት በተለይም በጤና እና በትምህርት ዘርፎች በርካታ የልማት ስራዎችን በጋራ ሲያከናውን መቆየቱ ይታወሳል።


