#FastMereja I ታዋቂው ጸሐፊ መጋቤ ምሥጢር አማኑኤል መንግሥተአብ ያዘጋጁትና “Prayer Book the Oriental Orthodox Churches” በሚል ርዕስ ለንባብ የበቃው አዲስ መጽሐፍ ዛሬ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አዳራሽ በታላቅ ሥነ-ሥርዓት ተመረቀ።
ዛሬ በተከናወነው በዚህ የምረቃ መርሐ-ግብር ላይ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የቤተክርስቲያን አገልጋዮች፣ ከፍተኛ ምሁራንና የጥበብ ሰዎች ተገኝተዋል። መጽሐፉ በዋናነት የእህት አብያተ ክርስቲያናት የሆኑትን የኢትዮጵያ፣ የግብፅ፣ የሶሪያ፣ የአርመን እና የኤርትራ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት የጸሎት ሥርዓት ላይ ትኩረት ያደረገ ሲሆን፣ በግዕዝ እና በእንግሊዘኛ ቋንቋዎች ተዘጋጅቶ የቀረበ ነው።
ደራሲው መጋቤ ምሥጢር አማኑኤል መንግሥተአብ ከዚህ ቀደም 13 መጻሕፍትን ለንባብ ያበቁ ሲሆን፣ ይህ አዲስ መጽሐፋቸው በዓይነቱ ለየት ያለና ለዓለም አቀፍ ምዕመናንም ጭምር ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል። መጽሐፉን በአማዞን ድረ-ገጽ እንዲሁም በአዲስ አበባ በሚገኙ የመጽሐፍት መሸጫ መደብሮች ማግኘት እንደሚቻል በምረቃው ወቅት ተመልክቷል።
በዚሁ የምረቃ መርሐ-ግብር ላይ በተጨማሪም የ98 ዓመቱ የዕድሜ ባለጸጋ እና እስካሁን ከ50 በላይ መጻሕፍትን ለንባብ ያበቁት አንጋፋው ደራሲ ርእሰ ሊቃውንት ክንፈርግብ ማርቆስ ተገኝተው “ሰለስቱ ሐዲሳት” እና “ሃይማኖተ አበው” የተሰኙ ሁለት ስራዎቻቸውን በጋራ አስመርቀዋል።
የመጽሐፉ ምረቃ በሊቃነ ጳጳሳት ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ የተከፈተ ሲሆን፣ በተጨማሪም በምሁራን የቀረበ ጥናታዊ ጽሑፍ፣ በበገና፣ በዝማሜና በቅኔ የታጀቡ መንፈሳዊ መርሐ-ግብሮች ታጅበዋል።
ይህ አዲስ የጸሎት መጽሐፍ የአምስቱን አብያተ ክርስቲያናት መንፈሳዊና ታሪካዊ አንድነት ከመዘከር ባለፈ፣ ለጸሎት ሥርዓታቸው ዓለም አቀፋዊ እውቅናን ለመስጠትና ለትውልድ ለማስተላለፍ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ተብሏል።




