banner

ናይጄሪያውያን በሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ግንባር ተገደሉ፤ መንግስት ለዜጎቹ ጥብቅ ማስጠንቀቂያ ሰጠ

#FastMereja I የናይጄሪያ መንግስት ዜጎቹ በከፍተኛ ክፍያ እና በተለያዩ ማታለያዎች ተታልለው ወደ ባዕድ ሀገራት የጦር ቀጠናዎች እንዳይገቡ ጥብቅ ማሳሰቢያ ሰጠ። ይህ ማስጠንቀቂያ የወጣው ሁለት ናይጄሪያውያን በሩሲያ እና ዩክሬን የጦር ግንባር ላይ መገደላቸውን ተከትሎ ነው።

እንደ ዩክሬን ባለስልጣናት መረጃ ከሆነ፣ ሀምዛት ኮላዎሌ እና እምባ ኡዶካ የተባሉ ሁለት ናይጄሪያውያን በጦርነቱ ቀጠና ውስጥ ህይወታቸው አልፏል። ግለሰቦቹ እ.ኤ.አ. በ2025 ከሩሲያ ጦር ሰራዊት ጋር ውል መፈረማቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ሞታቸውም በናይጄሪያ መንግስት ዘንድ ከፍተኛ ድንጋጤንና ስጋትን ፈጥሯል።

የናይጄሪያ የደህንነት ተቋማት ባደረጉት ምርመራ፣ ናይጄሪያውያን እና ሌሎች አፍሪካውያን ወደ ጦር ግንባር የሚሳቡት በቀጥታ ለውጊያ ሳይሆን፣ ከፍተኛ ክፍያ ያላቸው ሲቪል ስራዎች፣ የጥበቃ ስራዎች፣ የነፃ ትምህርት እድል፣ ወደ አውሮፓ በቀላሉ የመሰደድ እድሎች በመጠቀም ነው ተብሏል።

ይሁን እንጂ ዜጎቹ ውል ፈርመው መድረሻቸው ላይ ሲደርሱ፣ ያለምንም በቂ ስልጠና በቀጥታ ወደ ከባድ ውጊያ ቀጠናዎች እንደሚሰማሩ ሪፖርቶች ያመለክታሉ።

የናይጄሪያ መንግስት ይህንን ሁኔታ “እያደገ የመጣ አደገኛ አዝማሚያ” ሲል የገለጸው ሲሆን፣ ዜጎች በህገ-ወጥ መንገድ ወደ ባዕድ ሀገራት ግጭቶች እንዲገቡ የሚደረገው ጥረት እንዲቆም አሳስቧል። ማንኛውም ናይጄሪያዊ ከሀገር ውጭ የሚቀርቡ የሥራ ወይም የትምህርት እድሎችን ከመቀበሉ በፊት ህጋዊነታቸውን በሚገባ እንዲያረጋግጡና ከጥርጣሬ ነፃ እንዲሆኑ መንግስት መክሯል።

Leave a Comment