#FastMereja I አሜሪካ እና እስራኤል ዛሬ ቅዳሜ “የቅድመ መከላከል ጥቃት” ሲሉ በጠሩት ዘመቻ በኢራን መዲና ቴህራን እና በተለያዩ አካባቢዎች ላይ የተቀናጀ ጥቃት ሰንዝረዋል።
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ስምንት ደቂቃ በፈጀ የቪዲዮ ንግግራቸው “ከባድ ወታደራዊ ኦፕሬሽን” መጀመሩን አረጋግጠዋል። ትራምፕ በንግግራቸው “ኢራን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ እንዲኖራት ፈጽሞ አንፈቅድም” ካሉ በኋላ፣ “ለረጅም ጊዜ የቆየውን ሽብር ከእንግዲህ አንታገስም” ሲሉ አስታውቀዋል።
በቴህራን የሚገኙ የዓይን እማኞች የፍንዳታ ድምፅ መስማታቸውን የገለጹ ሲሆን፣ በማህበራዊ ሚዲያ የተሰራጩ ምስሎችም ከከተማዋ ጭስ ሲነሳ ያሳያሉ።
ጥቃቱን ተከትሎ ኢራን እና እስራኤል የአየር ክልላቸውን የዘጉ ሲሆን፣ የኢራን ባለስልጣናት የሀገሪቱ የበላይ መሪ አያቶላ አሊ ካሜኒ ወደ ደህንነቱ የተጠበቀ ሚስጥራዊ ስፍራ መዛወራቸውን ገልጸዋል።
ይህ ወታደራዊ እርምጃ የተወሰደው ኢራን የኒውክሌር ፕሮግራሟን ለማሳደግ የምታደርገው ጥረት በምዕራባውያን ዘንድ ከፍተኛ ስጋት በፈጠረበት ወቅት ነው። ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከጥቃቱ በፊት በነበረው ዕለት በሰጡት መግለጫ፣ ከኢራን ጋር የሚደረገው ድርድር ውጤት ባለማምጣቱ ደስተኛ እንዳልሆኑ ገልጸው ነበር። “በሰላማዊ መንገድ መፍታቱን እመርጥ ነበር፣ ነገር ግን እነሱ በጣም አስቸጋሪ እና አደገኛ ሰዎች ናቸው” ብለዋል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ በኢራን የሚገኘው የብሪታንያ ኤምባሲ ሰራተኞቹን ያስወጣ ሲሆን፣ በኢየሩሳሌም የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲም ሰራተኞቹና ቤተሰቦቻቸው በደህንነት ስጋት ምክንያት እስራኤልን ለቀው እንዲወጡ አዟል።
