banner

በምሥራቅ አርሲ በ21 ኦርቶዶክሳውያን ላይ የተፈጸመውን ግድያ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አወገዘች

​#FastMereja I የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት በምሥራቅ አርሲ ሀገረ ስብከት፣ ሽርካ ወረዳ፣ ጃዊ ቀበሌ በታጣቂዎች በተፈጸመ ጥቃት የ21 ኦርቶዶክሳውያን ሕይወት ማለፉን ተከትሎ የተሰማውን ጥልቅ ኀዘንና መከፋት ገለጸ።

​የካቲት 19 ለ 20 አጥቢያ በተፈጸመው በዚህ ዘግናኝ ጥቃት፦
​አንድ ካህን፣ ​ሁለት ሴቶች እና ​18 ወንድ ኦርቶዶክሳውያን በግፍ መገደላቸውን የሀገረ ስብከቱ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ ለጠቅላይ ጽሕፈት ቤቱ በላኩት ደብዳቤ አረጋግጠዋል።

​የጠቅላይ ጽሕፈት ቤቱ ዋና ሥራ አስኪያጅና የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አባ ሳዊሮስ በመግለጫቸው እንዳሳሰቡት፤ በጥቃቱ የተሰማቸው ኀዘን ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው፣ መንግሥት አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስድ ጥሪ አቅርበዋል።

​”በሀገረ ስብከቱ በተለያዩ ጊዜያት የሚፈጸመው ዘግናኝ ግድያ ኦርቶዶክሳውያን በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል በነጻነት የመኖርና ሃይማኖታዊ ሥርዓታቸውን የመፈጸም መብትን የሚጋፋ ነው” ያሉት ብፁዕ አባ ሳዊሮስ፤ የክልሉና የፌዴራል መንግሥታት ጉዳዩን በልዩ ሁኔታ በመከታተል የማያዳግም መፍትሔ እንዲሰጡ አሳስበዋል።

​ቤተክርስቲያኒቱ በአካባቢው ያለው ችግር ከመሠረቱ እስከሚፈታ ድረስ የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ እንደምትቀጥልም በመግለጫው ተመላክቷል። በመጨረሻም ሕይወታቸውን ላጡት ወገኖች የዘላለም ዕረፍትን፣ ለወዳጅ ዘመዶቻቸው ደግሞ መጽናናትን ተመኝተዋል።

Leave a Comment