#FastMereja I የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ክቡር ማህሙድ አሊ ዩሱፍ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ከእስራኤል ኃይሎች ጋር በመቀናጀት በኢራን ኢስላማዊ ሪፐብሊክ ውስጥ በሚገኙ ኢላማዎች ላይ የፈጸሙትን ወታደራዊ ጥቃት ተከትሎ ጥልቅ ስጋታቸውን ገለጹ።
ሊቀመንበሩ በዛሬው ዕለት የካቲት 21 ቀን 2018 ዓ.ም በሰጡት መግለጫ፣ ይህ እርምጃ በመካከለኛው ምስራቅ ያለውን ግጭት በከፍተኛ ሁኔታ የሚያባብስ መሆኑን ጠቁመዋል።
ሁሉም ወገኖች ከፍተኛ ራስን የመግታት እርምጃ እንዲወስዱ፣ ውጥረቱን በአስቸኳይ እንዲያረግቡ እና ቀጣይነት ያለው ውይይት እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል።
ማንኛውም እርምጃ በዓለም አቀፍ ህጎች እና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቻርተር መሠረት መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።
የግጭቱ መባባስ ለዓለም አቀፍ ሰላም ስጋት ከመሆኑም ባለፈ፣ በሃይል ገበያ፣ በምግብ ዋስትና እና በኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጫና እንደሚፈጥር ተገልጿል። በተለይም አሁን ላይ የኢኮኖሚ ጫና ባለባት አፍሪካ ላይ ጉዳቱ የበረታ እንደሚሆን ተጠቁሟል።
በኦማን ሱልጣኔት የሚመሩ ዓለም አቀፍ የሽምግልና ጥረቶች ቅድሚያ እንዲሰጣቸው እና ሰላም ሊመጣ የሚችለው በዲፕሎማሲ እንጂ በኃይል አለመሆኑን ሊቀመንበሩ በድጋሚ አረጋግጠዋል።
