banner

መንግስት የነዳጅ አቅርቦት እጥረትን ለመከላከል ጥብቅ የቁጥጥር መመሪያዎችን አስተላለፈ

#FastMereja | በኢትዮጵያ ነዳጅ እና ኢነርጂ ባለስልጣን የወጣ አዲስ መመሪያ፣ በመካከለኛው ምስራቅ በተፈጠረው ቀውስ ምክንያት ሊከሰት የሚችለውን የነዳጅ አቅርቦት እጥረት ለመከላከልና ስርጭቱን በቁጥጥር ስር ለማዋል ጥብቅ ውሳኔዎችን አስተላልፏል።

ባለስልጣኑ “የቁጠባ እርምጃዎችን ስለመውሰድ” በሚል ርዕስ ባወጣው መመሪያ፣ የነዳጅ ምርቶችን በጥንቃቄና በቁጠባ ጥቅም ላይ ማዋል አስፈላጊ መሆኑን ገልጿል። በዚህም መሰረት ለጸጥታ ተቋማት፣ ለልማት ፕሮጀክቶች፣ ለኤክስፖርት ኢንዱስትሪዎች እና ለግብርና ልማት ቅድሚያ እንዲሰጥ ታዟል።

በነዳጅ ማደያዎች ላይ የተላለፉ ዋና ዋና መመሪያዎች፦
• የነዳጅ ማደያዎች ለህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ለሚሰጡ ተሽከርካሪዎች ቅድሚያ መስጠት እንዳለባቸው ተገልጿል።

• ማንኛውም ተሽከርካሪ በፋብሪካ ከተገጠመለት ታንከር ውጭ፣ ተጨማሪ ታንከር ወይም በርሜል ይዞ ነዳጅ መቅዳት በጥብቅ ተከልክሏል። ይህን የሚያደርጉ አካላት ካጋጠሙ ማደያዎች ለጸጥታ አካላት እንዲጠቁሙ ታዟል።

• ነዳጅ የጫኑ ቦቴዎች በተፈቀደላቸው ቦታና በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ (Timing Arrival) መሰረት መድረሳቸው በቅርብ ክትትል እንዲደረግ መመሪያ ተሰጥቷል።

• ነዳጅን ለታለመለት ዓላማ ብቻ ማዋል እንደሚገባና በህገ-ወጥ የንግድ ስርዓት ውስጥ የሚሳተፉ አካላት በህግ ተጠያቂ እንደሚሆኑ ባለስልጣኑ አስጠንቅቋል።

ይህ መመሪያ በክልልና በከተማ አስተዳደር የንግድ ቢሮዎች እንዲሁም በነዳጅ አቅራቢ ድርጅት በኩል ተግባራዊ እንዲሆን የታዘዘ ሲሆን፣ አላማውም በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ሊከሰት የሚችለውን ጫና ቀድሞ ለመከላከል መሆኑ ተመልክቷል።

Leave a Comment