banner

“የንባብ ችግኝ በቀዳማይ ልጅነት መትከል”፦ 6ኛው ዓመታዊ የሕፃናት ንባብ ጉባኤ ተጀመረ፤ 20 ሺህ መጻሕፍትም ተመረቁ

#FastMereja | በኢትዮጵያ ለ22 ዓመታት የንባብ ባህልን ለማስፋፋት ሲሠራ የቆየው ኢትዮጵያ ሪድስ (Ethiopia Reads) ከትምህርት ሚኒስቴር እና ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ጋር በመተባበር ያዘጋጀውን 6ኛውን ዓመታዊ የሕፃናት ንባብ ጉባኤውን “የንባብ ችግኝ በቀዳማይ ልጅነት መትከል” በሚል መሪ ቃል በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ ኢንተር ሌግዥሪ ሆቴል ማካሄድ ጀምሯል።

በጉባኤው መክፈቻ ላይ ከአዲስ አበባ ቀዳማይ ልጅነት ልማት ቢሮ ጋር በመተባበር ያዘጋጃቸውን 20 ሺህ የሕፃናት መጻሕፍት አስመርቋል። እነዚህ 10 ዓይነት ርዕስ ያላቸውና በሁለት ቋንቋዎች (አማርኛና ኦሮምኛ) የተዘጋጁ መጻሕፍት፣ ለቀዳማይ ልጅነት የአእምሮ ዕድገት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳላቸው ተገልጾ በቀጣይ ወደ ጤና ተቋማት እንደሚሰራጩ ተጠቁሟል።

በዛሬው መርሃ-ግብር ላይ ከመንግስትና ከግል ዘርፍ የተውጣጡ ከ150 በላይ ተጋባዥ እንግዶችና የዘርፉ ባለሙያዎች ተገኝተዋል። በመድረኩም በሕፃናት የንባብ ልምድ ላይ ያተኮሩ ጥናታዊ ጽሑፎች የቀረቡ ሲሆን፣ ጥልቅ የፓናል ውይይቶችና የልምድ ልውውጦችም ተካሂደዋል።

ኢትዮጵያ ሪድስ እስካሁን በሀገሪቱ የተለያዩ ክልሎች ከ70 በላይ ቤተ-መጻሕፍትን በማቋቋም ከ1.5 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችን ተጠቃሚ አድርጓል። በተለይም በደቡብና በኦሮሚያ ክልሎች ትምህርት ቤት መሄድ ለማይችሉ 14 ሺህ ሕፃናት በፈረስና በአህያ በታገዘ ተንቀሳቃሽ የንባብ አገልግሎት መጻሕፍትን እስከ መንደራቸው ድረስ በማድረስ የሚታወቅ አንጋፋ ድርጅት ነው።

ይህ ጉባኤ ለወደፊቱ የተሻለ የእውቀት ትውልድ ለመቅረጽ የሚያስችሉ ጠቃሚ ግብዓቶችና ምክረ-ሀሳቦች ይገኙበታል ተብሎ ይጠበቃል።





Leave a Comment