banner

እናት ባንክ የሴቶች የፋይናንስ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ‘የሥርዓተ ፆታ ቦንድ’ ሊጀመር ነው!

#Fastmereja:እናት ባንክ የሴት አመራሮችን ክህሎትና ተሳትፎ ለማሳደግ ያለመ “High Level Women Leadership” የተሰኘ የፓናል ውይይት በዲሊዮፖል ሆቴል አካሄደ።

የባንኩ የቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሮ አስቴር ሰለሞን በመክፈቻ ንግግራቸው እንደገለፁት፤ ባንኩ ባለፉት 13 ዓመታት የሴት ሰራተኞችን አቅም በማሳደግና ወደ አመራር በማምጣት የደንበኞችን አገልግሎት ማሻሻል መቻሉን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅትም የባንኩን እድገት ለማፋጠን በሚደረገው ጥረት ውስጥ ሴት ሰራተኞች ግንባር ቀደም ሚና እየተጫወቱ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት እናት ባንክ ካሉት ከ2,000 በላይ ሰራተኞች መካከል 952ቱ ሴቶች ሲሆኑ፣ ከ11 የቦርድ አባላት መካከል 7ቱ ሴቶች መሆናቸዉ የተገለፀ ሲሆን በተጨማሪም በከፍተኛ የሥራ ካውንስል ውስጥ የሴቶች ድርሻ 44 በመቶ መድረሱ የባንኩን አካታችነት እንደሚያሳይ ተገልጿል።

ባንኩ ላሳየው ተከታታይነት ያለው የሴቶች ተሳትፎ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክና በዓለም ባንክ የጋራ ምዘና (Gender Scorecard) “ፈር ቀዳጅ ባንክ”(The First and Only Transformational Bank) የሚል እውቅና ማግኘቱም በዝግጅቱ ላይ ይፋ ሆኗል።

ይህ እውቅና የተሰጠው ባንኩ በፋይናንስ አካታችነት፣ በሴቶች የሥራ ዕድገትና ለሴቶች ተብለው በተቀረጹ የብድርና ቁጠባ አገልግሎቶች ባከናወነው ውጤታማ ተግባር መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

በቀጣይነትም በኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚተገበረውንና የሴቶችን የፋይናንስ ተጠቃሚነት በከፍተኛ ደረጃ ያሳድጋል የተባለለትን የሥርዓተ ፆታ ቦንድ (Gender Bond) ወደ አገልግሎት ለማስገባት ዝግጅት መጠናቀቁ ተገልጿል።

በመድረኩ ላይ ዶ/ር ተዋበች ቢሻው፣ ወ/ሮ ናስሪን መሐመድ እና ዶ/ር ገመቹ ዋቅቶላ የካበተ የሥራና የሕይወት ተሞክሮአቸውን ለታዳሚዎች አጋርተዋል።

እናት ባንክ በአሁኑ ወቅት በመላ ሀገሪቱ 222 ቅርንጫፎችን በመክፈትና የዲጂታል ባንኪንግ አገልግሎቱን በማስፋፋት ተደራሽነቱን እያሳደገ ይገኛል።





Leave a Comment